ዲሞክራሲና የማህበራዊ ዋስትና ሥርዓት

ዲሞክራሲና የማህበራዊ ዋስትና ሥርዓት


ኖርዌይ ዲሞክራሲያዊ ሃገር ናት። ዲሞክራሲ የሚለው ቃል የመጣው ከግሪክ ቋንቋ ሲሆን፣ ትርጉሙም ̋̋̋በህዝብ የሚመራ ̋ ማለት ነው። ህዝቡ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እና ተወካዮችን ለተወካዮች ምክር ቤት፣ ለዞንና ለወረዳ ምክር ቤት በመምረጥ የኖርዌይ ፖለቲካን ይመራል። በዚህ መልኩ ወሳኞቹ ብዙሃኑ ይሆናሉ። ይሁን እንጂ አንድ ሊታወስ የሚገባው በጣም አስፈላጊ መርህ የአብዛኛውን ህዝብ ድምፅ ያገኘው አካል ፖሊሲዎችን በሚያወጣበት ጊዜ የንኡሳኑን ሃሳብ ከግምት ውስጥ ማስገባት አለበት።

በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ውስጥ ዜጐች አንዳንድ መብቶችና ነፃነቶች አሏቸው፡-

ሰብዓዊ መብቶች

FN-flagget FN-bygningen i New York
ሰብዓዊ መብቶች ማንኛውም ሰዉ የሰዉ ልጅ በመሆኑ ብቻ ያሉን መብቶች እንጂ በዓለም በምንኖርበት ቦታ ወይም በምንከተለው ሃይማኖት ወይም በብሔር የሚወሰን አይደለም። ስለዚህ ሰብዓዊ መብቶች ዓለም አቀፋዊ መብቶች ይባላሉ። ሰብዓዊ መብቶች በዋናነት የሚያተኩሩት በግለሰቦችና በመንግሥት መካከል ባለው ግንኙነት ላይ ነው።

በ1948 ዓ.ም የተመድ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ ፀደቀ። ሰብዓዊ መብቶች ለሁሉም ሰዎች የሚተገበሩ ሲሆን፣ የሚከተሉትን በግልፅ ያካትታሉ፡-

 • ሁሉም ሰዎች ነፃ ሆነው እኩል ሰብዓዊ ክብር እና ሰብዓዊ መብቶች ይዘው ነዉ የተወልዱት።
 • ሁሉም ሰዎች በመካከላቸው የፆታ፣ የሃይማኖት፣ የዘር፣ የፖለቲካ አመለካከቶች፣ የብሔር ወዘተ. ልዩነቶች ሳይደረጉ እኩል ሰብዓዊ መብቶች አላቸው።
 • ሁሉም ሰዎች በነፃነት የመኖርና የግል ደህንነት የማግኘት መብት አላቸው።
 • ማንኛውንም ዓይነት ስቃይ ማድረስ የተከለከለ ነው።
 • ሁሉም ሰዎች የህግ ዋስትና ሊኖራቸው ይገባል።
 • ሁሉም ሰዎች ነፃና ምስጢራዊ በሆነ ምርጫ ላይ ድምፅ በስጠት የሃገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ ላይ ተፅዕኖ የማሳደር መብት አላቸው።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች አብዛኛዎቹ ክፍሎች በኖርዌይ ህጐች ውስጥ ተካትተዋል።

እኩልነት

Personar i rullestol Homofilt par To eldre damer på tur Fem barn sammen

በተለምዶ የእኩልነት ፅንሰ ሀሳብ ያተኩር የነበረው ወንዶችና ሴቶች እኩል መብቶችና ዕድሎችን ማግኘት ላይ ነበር። አሁን ግን እኩልነት ከዚህ የሰፋ ነገር ላይ ያተኩራል። ስለዚህ የዕድሜ፣ የብሔር፣ የአካል ጉዳት፣ የፆታ፣ የሃይማኖትና የፍቅር አጋር ምርጫ ልዩነት በመካከላቸው ሳይደረግ ሁሉም ሰዎች እኩል መብቶችና ዕድሎች ሊያገኙ ይገባል።

እኩልነት ከሚያተኩርባቸዉ ጉዳዮች ዉስጥ የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያክል፡-ተፅዕኖ ለመፍጠርና ለውጥ ለማምጣት እኩል ዕድል ማግኘት፣ ፍትሃዊ የኃላፊነትና የስራ ጫናን ክፍፍል ማድረግ እና እንዲሁም ሰዎች ጥቃት ወይም በደል ይደርስብኛል የሚል ሥጋት እንዳይኖራቸው ማድረግ ናቸዉ።

ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት

ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ማለት ማንኛውም ሰው ምንም ዓይነት ሥጋት ሳያድርበት በፖለቲካዊ፣ በሃይማኖታዊና በሌሎች ጉዳዮች ላይ የመሰለውን አመለካከት በነፃነት የመግለፅ፣ ከሌሎች ጋር በጉዳዮቹ ላይ በነፃነት የመከራከርና የመፃፍ መብት መኖር ማለት ነዉ።

ይሁን እንጂ በቃልና በፅሑፍ ሃሳብን በመግለፅ ነፃነትና ስለሌሎች ሰዎች መጥፎ ነገሮችን በመናገር መካከል ገደብ አለ። ስለዚህ ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ላይ ገደብ የሚጥሉ በርካታ ህጐች አሉ። ለምሳሌ በሌሎች ሰዎች ላይ የዘረኝነትና የጥላቻ አስተያየት በቃልም ሆነ በፅሑፍ በይፋ መስጠት በህግ የተከለከለ ነው።

ሐሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት ለግለሰቦች እንዲሁም ለሬዲዮ፣ ለቴሌቪዥንና ለጋዜጦችም የተሰጠ መብት ነው።

የህግ ዋስትና

ኖርዌይ ውስጥ ዜጐች ጥሩ የህግ ዋስትና አላቸው። ይህም የሚከተሉትን ያካትታል፡-

 • ማንኛውም ሰው የፍርድ ሂደት ሳይደረግለት በእስራት ሊቀጣ አይችልም። የፍርድ ሂደት ነፃ የሆኑ ዳኞች የተከሰሰው ሰው ጥፋተኛ መሆኑን ወይም አለመሆኑን የሚወስኑበትና ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ ተከሳሹ መቀጣት የሚገባውን ፍርድ የሚወስኑበት ሂደት ማለት ነው። ይሁን እንጂ ወንጀል ሰርተዋል ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች ፍርድ ቤት ከመቅረባቸው በፊት ፖሊስ ወንጀሉን እስኪያጣራ ድረስ በቁጥጥር ሥር ሊውሉ ይችላሉ።
 • በወንጀል የተከሰሱ ሰዎች በሙሉ ጠበቃ የማግኘት መብት አላቸው።
 • ፍርድ ቤቶች ነፃነት አላቸው። ስለዚህ በአንድ ጉዳይ ላይ በሚሰሩበት ጊዜ በማናቸውም ፖለቲከኞች፣ መገናኛ ብዙሃን ወይም በሌሎች ቡድኖች ተፅዕኖ ሥር መውደቅ የለባቸውም። የተወካዮች ምክር ቤት፣ መንግሥት ወይም ባለሥልጣናት በፍርድ ቤት ውሳኔ ውስጥ ጣልቃ መግባት አይችሉም።
 • የትኛዉም ህግ ወደኋላ ተመልሶ አይሰራም። ይህም ማለት አንድ ሰው የወንጀል ድርጊት መፈፀም አለመፈፀሙን ለመወሰን ወይም ቅጣት ለማስተላለፍ ተግባር ላይ የሚውለው ወንጀሉ በተፈፀመበት ጊዜ የነበረው ህግ ይሆናል።

የሃይማኖትና የእምነት ነፃነት

ማንኛውም ሰው የመረጠውን ሃይማኖት ወይም እምነት የመያዝ ወይም የመቀበል ወይም የመከተል መብት አለው። ማንኛውንም ሰው በኃይል በማስገደድ ከአንድ የሃይማኖት ተቋም ወይም ቡድን ማስወጣትም ሆነ ማስገባት አይቻልም። አንድ ሰው ዕድሜው 15 ዓመት ከሞላው ከሃይማኖት ተቋም ወይም ከእምነት ማህበራት በራሱ ፈቃድ የመልቀቅ መብት አለው። ማንኛውም ሰው በሃይማኖቱ ምክንያት ሊሳደድ ወይም ሊቀጣ አይገባውም።

ማንኛውም ሰው የመረጠውን ሃይማኖት ወይም መንፈሳዊ ድርጅት የመከተል መብት እንዳለው ሁሉ የትኛውንም ሃይማኖት ወይም እምነት ያለመከተልም ነፃነት አለው።

የመደራጀት ነፃነት

የመደራጀት ነፃነት በርካታ ነገሮችን ይይዛል። ከእነዚህ ውስጥ ዋና ዋናዎቹ፡-

 • ያለምንም የመሳደድ ወይም የቅጣት ፍርሃት ማንኛዉም ሰዉ የፖለቲካ ፓርቲ ወይም የተለያዩ ማህበራት አባል የመሆን መብት አለዉ።
 • ያለምንም የመሳደድ ወይም የቅጣት ፍርሃት ማንኛዉም ሰዉ የሠራተኛ ማህበር አባል የመሆን መብት አለዉ። በአንዳንድ ሁኔታዎች ደግሞ ሥየራ ማቆም አድማ ማድረግ መብት አለዉ።
 • ማንኛዉም ሰዉ ህጋዊ በሆኑ ሰላማዊ ሰልፎች አማካኝነት ሃሳብን የመግለፅ መብት አለዉ።

መረጃ

የመምረጥ መብት

 • በኖርዌይ የመምረጥ መብት እድሜ 18 ነው።
 • በፓርላማ ምርጫ ለመሳተፍ የኖርዊጂያን ዜጋ መሆን አለብዎት።
 • በዞንና በወረዳ ምርጫ ድምፅ ለመስጠት ከምርጫው በፊት ሶስት ዓመት በኖርዌይ መኖር ይኖርብዎታል።
 • በ1913 ዓ. ም ሴቶች የመምረጥ መብት ካገኙበት ጊዜ አንስቶ በኖርዌይ ሁሉም የመምረጥ መብት አለው።

የዘረኝነት አንቀፅ (የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀፅ 185 አ)

«በአደባባይ በመለስተኛም ይሁን ሆን ብሎ የዘር መለየት ወይም ጥላቻ የሚያፀባርቅ ሰው በገንዘብ ወይም እስከ 3 ዓመት በእስራት ይቀጣል። ልክ እንደ ማስታወቂያ ብዙሃን በአንቀፅ 7 ቁ. 2 አንድ ጉዳይ ብዙ ህዝብ ጋር ከደረሰ ለህዝብ እንደተነገረ ይቆጠራል። ምልክቶችን መጠቀምም እንዲሁ እንደማስታቂያ ይቆጠራል። በዚህ ጉዳይ ላይ የተባበረም በተመሳሳይ ሁኔታ ይቀጣል። በዘር መለየት ወይም ጥላቻ ማለት አንድን ሰዉ ማስፈራራት ወይም ማጥላላት፣ ጥላቻን መግለፅ፣ ማሳደድ ወይም ማግለል ነው። ይህም ከሚከተሉት የተነሳ ከሆነ፣

 • ሀ. የቆዳ ቀለም ወይም አገር ወይም ዘር
 • ለ. ሀይማኖት ወይም እምነት ወይም
 • ሐ. ከተመሳሳይ ጾታ ጋር ግብረ ሥጋ ግንኙነት ስለምያደርግ ወይም ከአኗኗሩ የመሳሰሉ»

የዘረኝነት አንቀፅ ብዙ ክርክር ተደርጎበታል። የተወሰነ ሰው እንዲሰረዝ ይፈልጋል፣ ምክያቱም የራስን ሃሳብ ከመግለፅ ጋር ይቃረናል። በዚህ አንቀፅ የተቀጡት በጣም ጥቂቶች ናቸው።

ጁላይ 22 ቀን 2011 ዓ.ም

በኖርዊጂያን የቅርብ ጊዜ ታሪክ ውስጥ ጁላይ 22 ቀን 2011 ዓ.ም የሚታወስ ቀን ነው። ያን ቀን ኖርዌይ ለቴረር ተጋለጠች። በኦስሎ ቤተ መንግስት በፈነዳዉ ቦምብ 8 ሰዎች ሞቱ፣ በኡቶያ ደግሞ በአንድ የወጣቶች ፖለቲካ ካምፕ 69 ሰዎች በጥይት ተገደሉ። በተጨማሪም ብዙ ሰዎች ቆሰሉ። ሁለቱንም ወንጀል የፈፀመው አንድ ሰው ነው።