ታሪክ፣ ህብረተሰብና የኑሮ ሁኔታ

ባህልና አመት በአል

ዝክረ በዓላት

አዲስ ዓመት
አዲስ ዓመት የሚጀምረው ጃንዋሪ 1 ላይ ነው። በዚህ ዕለት አብዛኛዎቹ የንግድ ተቋማት ዝግ ሲሆኑ፣ ብዙ ሰዎች ሥራ አይገቡም፤ ተማሪዎችም ትምህርት አይኖራቸውም።

የሴቶች ቀን
ማርች 8 (የካቲት 28) ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ነው። በ197ዐዎቹ ውስጥ ለሴቶች እኩልነትና ለሴቶች መብቶች መከበር ብዙ ሰዎች ታግለዋል። ከ1972 ጀምሮ ኖርዌይ በየዓመቱ የሴቶችን ቀን በማክበር ላይ ትገኛለች። ማርች 8 የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ዝግ የሚሆኑበት በዓል አይደለም።

የትንሳኤ በዓል
የትንሳኤ በዓል መጋቢት ወይም ሚያዝያ ውስጥ ይከበራል። በዓሉ የሚውልበት ትክክለኛ ቀን ከዓመት ዓመት ይለያያል።
ትንሳኤ የክርስትና እምነት ተከታዮች በዓል ነው። ነገር ግን ብዙ ሰዎች ይህን በዓል በዋናነት የሚያከብሩት በሃይማኖታዊነቱ ሳይሆን ከረጅም የክረምት ጊዜ በኋላ ለበርካታ ቀናት ከሥራ ነፃ የሚሆኑበት ጊዜ በመሆኑ ነው።

ጸሎተ ሐሙስ፣ ስቅለት እና የትንሳኤ ቀን የበዓል ቀናት ናቸው። በነዚህ ቀናት የንግድ ተቋማት ይዘጋሉ፤ ቡዙ ሠራተኞችም ስራ ስለማይገቡ ይህን አጋጣሚ ተጠቅመው የተጨማሪ ቀናት እረፍት ይወስዳሉ። ልጆችም የትንሳኤ ሰሞን ትምህርት አይኖራቸውም።

በዓለ እርገት እና በዓለ አምሳ/ጴንጤቆስጤ/
ከትንሳኤ በዓል በዋለ በ4ዐኛው ቀን በዓለ እርገት ሲከበር ትንሳኤ በዋለ በ5ዐኛው ቀን ደግሞ በዓለ አምሳ/ጴንጤቆስጤ (መንፈስ ቅዱስ የወረደበት ቀን) ይከበራል። እነዚህ በዓላት የክርስትና ኃይማኖት በዓላት ናቸው። በዓለ እርገት እና በዓለ አምሣ ማግስት ያለው ቀን የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ዝግ ናቸዉ።

ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን
ዓለም አቀፍ የሠራተኞች ቀን ሜይ 1 ይከበራል።
በዚህ ቀን በርካታ ሠራተኞች ሠላማዊ ሰልፍ በማድረግ በሚያሳስቧቸው የፖለቲካ ጥያቄዎች ላይ ድምፃቸውን ያሰማሉ።
በሜይ 1 የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ዝግ ናቸዉ።

ብሔራዊ ቀን
17.mai 17.mai 17.mai

የኖርዌይ ብሔራዊ ቀን የሚከበረው ሜይ 17 ነው። ይህ ቀን የሚዘከረው ሃገሪቱ በሜይ 17፣ 1814 ዓ.ም የመጀመሪያውን ህገ-መንግሥት ያፀደቀችበትን ዕለት በማሰብ ነው።

ሜይ 17 በተለይ የልጆች ቀን ነዉ። በዚህ ዕለት ሁሉም የመዋፅለ-ህፃናትና የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች የኖርዌይን ባንዲራ እያውለበለቡና እየዘመሩ ሰልፍ ያደርጋሉ። አብዛኛዎቹ ልጆች ለዕለቱ በዓል የሚሆን ልብስ ለብሰው ይወጣሉ። ሰልፉን የሚመሩት ደግሞ ተመሳሳይ የደንብ ልብስ የለበሱ የማርሽ ሙዚቀኞች ናቸው። ብዙ ልጆች የማርሽ ሙዚቃ ቡድን ውስጥ ይሳተፋሉ።

በዚህ ዕለት ልጆች የፈለጉትን ያህል አይስክሬምና ሌሎች ጣፋጭ ምግቦችን መመገብ ስለሚፈቀድላቸው በዓሉን የሚጠብቁት በናፍቆት ነው።
በሜይ 17 የመንግሥት መስሪያ ቤቶች ዝግ ናቸዉ።

የገና በዓል

የገና በዓል የሚከበረው በታህሣሥ ወር ነው። ገና የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል የሚታሰብበት የክርስትና እምነት ተከታዮች በዓል ነው። ገና እንዲሁም የገና ክብረ በዓል በብዙ ሰዎች ዘንድ የሚወደድ በዓል ነው። በመሆኑም በዓሉ በተለይ የቤተሰብ ክብረ በዓል ነው።

የገና በዓል የሚውለው እጅግ ቀዝቃዛና ጨለማ በሆነው የክረምት ወቅት በመሆኑ ክብረ በዓሉ ለብዙ ሰዎች ብርሃንና ሙቀት እንደማግኘትአድርገው ያስቡታል። ኖርዌይ ክርስትናን ከመቀበሏ በፊት በነበሩት ዓመታትም ቢሆን ትልልቅ ክብረ በዓላት ይደረጉ ነበር። ይህ ምናልባትም የወቅቱን ጨለማ በብርሃን ለማድመቅ በሚል ሳይሆን አይቀርም።

የገና ዋዜማ የሚውለው ዲሴምበር 24 ነው። በዚህ ዕለት ከቤተሰብ ጋር በመሰባሰብ ባህላዊ የገና እራት አብሮ መብላት የተለመደ ነው። የሃገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች የተለያዩ ልማዶች አሏቸው። ብዙ ሰዎችም የራሳቸውን ልማድ የመከተል ጠንካራ ስሜት አላቸው። በገና ዋዜማ የገና ስጦታዎችን እርስ በርስ መለዋወጥ የተለመደ ነገር ነው።

ከገና በፊት ባሉት ሳምንታት ብዙ ሰዎች መልካም የገና በዓል ምኞት መግለጫ ካርዶችን፣ የኢሜይል ወይም ሌሎች መልዕክቶችን ለወዳጅ ዘመዶቻቸው ይልካሉ። በገና ሰሞን ትምህርት ቤቶችና መሥሪያ ቤቶች ዝግ ስለሚሆኑ ልጆችና በርካታ ሠራተኞች እረፍት ይወስዳሉ። በገና ክብረ በዓል ሰሞን የንግድ መደብሮች ለተወሰነ ቀናት ዝግ ናቸው።

የአዲስ ዓመት ዋዜማ
Fyrverkeri

የአዲስ ዓመት ዋዜማ የሚውለው ዲሴምበር 31 ሲሆን፣ ወዳጅ ዘመድ በአንድነት ተሰብስበው ርችት በመተኮስና በተለያዩ መንገዶች ያከብሩታል። እኩለ ሌሊት ላይ ሰማዩ በርችት ሲደምቅ እጅግ የሚያስደስት ስሜት ይፈጥራል።
የአዲስ ዓመት ዋዜማ ሥራ የሚዘጋበት ቀን አይደለም።

የዘመን መቁጠሪያ ካሌንደርን የማይከተሉ በዓላት

የልደት ቀን
Bursdagsbarn som blåser ut lys på kaka

የልደት በዓልን በተለይ ለልጆች ማክበር የተለመደ ነው። ልጆች የልደት በዓላቸውን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ከማክበር በተጨማሪ ጓደኞቻቸውን ከመዋዕለ-ህፃናት ወይም ከትምህርት ቤት በመጥራት አብረው ያከብራሉ።

አብዛኛውን ጊዜ ልጆች የልደት በዓላቸው የሚከበርላቸው በመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ በሌሎች ቦታዎች ለምሳሌ በፒዛ ቤት፣ በመዋኛ ሥፍራ ወይም በልጆች መዝናኛ ሥፍራ ሊከበር ይችላል።
በልደት በዓል ላይ የሚገኙ እንግዶች መጠነኛ ስጦታ ልደቱን ለሚያከብረው ልጅ ይዘው ይመጣሉ።

ሰርግ
Brudepar

በየዓመቱ ወደ 23,ዐዐዐ የሚጠጉ ጥንዶች ኖርዌይ ውስጥ ጋብቻ ይፈፅማሉ። ከእነዚህ ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ጋብቻቸውን የሚያደርጉት በቤተ ክርስቲያን ሲሆን ቀሪዎቹ ደግሞ በማዘጋጃ ቤት ወይም ጉዳዩ በሚመለከተው የመንግሥት መሥሪያ ቤት ውስጥ ነው። ኖርዌይ ውስጥ የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻም ይፈቀዳል። አብዛኞቹ ሙሽሮች ሰርጋቸውን ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር በመሆን ያከብራሉ።
በሰርግ ላይ የታደሙ እንግዶች እንዲሁም ሙሽራውንና ሙሽሪትን የሚያውቁ ሌሎች ሰዎች ወይም ቤተሰቦቻቸው ለጥንዶቹ ስጦታ መስጠት የተለመደ ነው።

ክርስትና
በየዓመቱ ኖርዌይ ውስጥ 6ዐ,ዐዐዐ የሚደርሱ ህፃናት ይወለዳሉ። ከእነዚህ ውስጥ ከ5ዐ እስከ 6ዐ በመቶ የሚደርሱት በህፃንነታቸው በቤተክርስቲያን ሥርዓተ-ጥምቀት ክርስትና ይነሳሉ። አንድ ህፃን ክርስትና ሲነሳ የቤተክርስቲያን አባል ይሆናል። የህፃኑን ክርስትና መነሳት ወይም አለመነሳት የሚወስኑት ቤተሰቦቹ ናቸው።

ህፃን ልጅ ክርስትና ሲነሳ ቤተሰቦቹ ትልቅ ግብዣ የሚያዘጋጁ ሲሆን ለህፃኑም ስጦታዎች ይሰጣሉ። ልጆቻቸውን ቤተክርስቲያን ወስደው ክርስትና ያላስነሱ ቤተሰቦች ሃይማኖታዊ ያልሆነ በዓል ለልጃቸው ያዘጋጃሉ። አንዳንዶቹ ሙሉ በሙሉ የግል በሆነ መንገድ ሲያከብሩ ሌሎች ደግሞ ሃይማኖታዊ ባልሆነ መልኩ በተዘጋጀ የስያሜ ድግስ ይሳተፋሉ።

የእምነት ማረጋገጥ በዓል

ልጆች ከ14 – 15 ዓመት ዕድሜ ላይ ሲደርሱ ክርስትናን የመቀበል ምርጫ ማድረግ ይችላሉ። የበዓል ስርዓቱን በቤተ ክርስቲያን ለማድረግ ከመረጡ የቤተክርስትያን አባል ሆነው መቀጠል እንደሚፈልጉ አረጋገጡ ማለት ነው። ክርስትና መቀበልን የማረጋገጥ ሥርዓት ልጆች በህጻንነታቸዉ የተነሱትን ክርስትና የሚያፀኑበት መንገድ ነዉ።

ባለፉት አስርታት ዓመታት ስነ ሰብዓዊ እምነት የማረጋገጥ በዓል ማለትም ሃይማኖታዊ ይዘት የሌላቸው በዓላት ከግዜ ወደ ጊዜ እየትለመዱ መጥተዋል። እምነት የማረጋገጫ በዓል ከመደረጉ በፊት ወጣት ልጆች የዝግጅት ትምህርት በቤተክርስቲያን ወይም በሌላ ርእዮተ አለማዊ ተቋም ውስጥ ይከታተላሉ። ክርስትና መቀበላቸውን የሚያረጋግጡት ልጆች ስለ ክርስትና በመማር በግብረ ገብነትና በሞራል ጉዳዮች ላይ ውይይት ያደርጋሉ። ስነ ሰብዓዊ እምነትን የሚመርጡ ደግሞ ስለ ሥነ-ሰብ ይማራሉ እንዲሁም ስለ ርእዮተ አለም፣ ሥነምግባር እና ሞራል ይወያያሉ።

አንድ ወጣት የእምነት የማረጋገጥ ሥርዓት ሲፈፅም ወላጆች ትልቅ ግብዣ ያዘጋጃሉ፤ ለአረጋጋጩም ስጦታ ይሰጣል።
6ዐ በመቶ የሚጠጋው የኖርዌይ ወጣት እምነት የማረጋገጥ ሥርዓትን በቤተክርስቲያን ያከናዉናል። 2ዐ በመቶ የሚሆነዉ ስነ ሰብዓዊ እምነት የማረጋገጥ ሥርዓትን ይመርጣል። ወደ 2ዐ በመቶ የሚጠጋው ደግሞ ምንም አይነት የማረጋገጫ ሥርዓት ውስጥ አይሳተፍም።

ሥርዓተ ቀብር
Kiste

ኖርዌይ ውስጥ በየዓመቱ 4ዐ ዐዐዐ የሚጠጉ ሰዎች ይሞታሉ። ከእነዚህ ውስጥ 85 በመቶ የሚሆኑት ሥርዓተ ቀብራቸው የሚፈፀመው በቤተ ክርስቲያን ስርዓት ነው። ይህ ማለት የቀብር ሥርዓቱ የሚመራው በካህን ነው።

ሁለት ዋና ዋና የሥርዓተ ቀብር ዓይነቶች አሉ። እነዚህም ሬሳን የመቅበር ሥርዓትና ሬሳን የማቃጠል ሥርዓት ናቸው። የመጀመሪያው የቀብር ሥርዓት የሚከናወነው ሬሳውን ሳጥን ውስጥ በማሸግና በመቅበር ሲሆን፣ በሁለተኛው ሥርዓት ደግሞ ሬሳውን በማቃጠልና አመዱን በዕቃ ውስጥ በማድረግ መቅበር ነው።

ሬሳን አቃጥሎ አመዱን መቅበር ኖርዌይ ውስጥ ይበልጥ የተለመደ ሆኗል። ወደ 4ዐ በመቶ የሚጠጉ ሟቾች የሚቀበሩት በዚሁ ሥርዓት ነው።

መረጃ

ጃኗሪ 1 ቀን አዲስ ዓመት ነው

ማርች 8 ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ነው

በማርች/አፕሪል ፋሲካ ነው

ፋሲካ ወጥቶ ከ40 ቀን በኋላ ክርስቲ ህመልፋርትስ ቀን

ከፈሲካ 50 ቀን በኋላ ፕንሴ በዓል

ሜይ አንድ ቀን ዓለም አቀፍ የወዝ አደሮች ቀን

ሜይ 17 ቀን የኖርዌይ አገር አቀፍ በዓል

ደሰምበር 24 ቀን የገና ዋዜማ

ደሰምበር 31 ቀን የአዲስ ዓመት ዋዜማ