መንግስት፣ ዞን ፅህፍት ቤትና ወረዳዎች
ኖርዌይ ውስጥ 11 ዞኖች እና 356 ወረዳዎች አሉ። (ኦስሎ እንደ ዞንም እንደ ወረዳ ትቆጠራለች) ።
ዞኖች እና ወረዳዎች መልክአ ምድራዊ ቦታዎችና የፖለቲካ አስተዳደር አካላት ናቸው። ምንም እንኳ መንግሥት በርካታ ውሳኔዎችን የሚያስተላልፍ ቢሆንም ዞኖችና ወረዳዎች ራሳቸው የሚወስኑባቸው ብዙ ጉዳዮች አሏቸው። መንግሥት የተለያዩ መዋቅሮችን ለዞኖች እና ለወረዳዎች ያቀርባል። መንግሥት የመላ ሃገሪቱ ገዥ ሲሆን፣ ዞኖችና ወረዳዎች ግን ማስተዳደር የሚችሉት የራሳቸውን አካባቢ ብቻ ነው።
ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ አመራር
መንግሥት፣ ዞኖችና ወረዳዎች የሚመሩት በህዝብ በተመረጡ ፖለቲከኞች ነው። በመሆኑም ፖለቲከኞቹ በርካታ ጉዳዮች ላይ በመወያየት በተለያዩ ቦታዎች ተግባራዊ የሚደረጉ ፖሊሲዎችን ይወስናሉ። ነገር ግን ፖሊሲዎቹን የሚያስፈፅሙት የመንግሥት፣ የዞኖችና ወረዳዎች ሰራተኞች ናቸው።