ዲሞክራሲና የማህበራዊ ዋስትና ሥርዓት

የተወካዮች ምክር ቤትና መንግስት

የተወካዮች ምክር ቤት

Stortingsbygningen - © Stortingsarkivet/ foto: Teigens fotoatelier as.
የኖርዌይ የተወካዮች ምክር ቤት ስቶርቲንግ ተብሎ ይጠራል። ምክር ቤቱ በየአራት ዓመቱ በህዝብ የሚመረጡ 169 ተወካዮች አሉት። እነዚህ ተወካዮች የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚወክሉ ናቸው። በኖርዌይ ትልቁን የመንግሥት ሥልጣን የያዘው የተወካዮች ምክር ቤት ነው።

የተወካዮች ምክር ቤት አበይት ሥራዎች የሚከተሉት ናቸው፡-

  • አዲስ ህጐችን ማውጣትና የቆዩ ህጐችን ማሻሻል
  • የሃገሪቱን በጀት ማፅደቅ
  • መንግሥትንና የመንግሥት አስተዳደርን መቆጣጠር
  • በፖለቲካዊ ጉዳዮችና በትልልቅ ፕሮጀክቶች ላይ መወያየት

Stortingssalen - © Stortingsarkivet/ foto: Teigens fotoatelier as.

በተወካዮች ምክር ቤት የሚደረጉ የፖለቲካ ክርክሮች ለህዝብ ክፍት ናቸው። ማንኛውም ፍላጐት ያለው ሰው በምክር ቤቱ ተገኝቶ ውይይቶቹን ማዳመጥ ይችላል። ነገር ግን ህዝቡ በተወካዮች ምክር ቤት ውይይት ላይ የመናገርም ሆነ አስተያየት የመስጠት መብት የለውም።ጥያቄ ማቅረብ የሚፈልግ ሰው ጥያቄውን በኢ-ሜይል ወይም በፖስታ ለተወካዮች ምክር ቤት አባላት መላክ ይችላል። የሁሉም ተወካዮች አድራሻዎችና ሌሎች መረጃዎችን ከዚህ ድረ-ገፅ ማግኘት ይቻላል፡-stortinget.no.

መንግሥት

የሚመሰረተው መንግሥት ሚኒስትሮች (የእያንዳንዱ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት የፖለቲካ መሪዎች) እና ጠቅላይ ሚኒስትርን ይይዛል።ከመንግሥት ሥራዎች ውስጥ አንዱ የአዳዲስ ህጐች ረቂቅ ሃሣብ ማቅረብና በሥራ ላይ ያሉትን ህጐች እንዲቀየሩ መጠየቅ ነው። ይሁን እንጂ አዲስ ህጐችን የሚያፀድቀውና የህግ ማሻሻያ የሚያደርገው የተወካዮች ምክር ቤት ነው።

መንግሥት በተወካዮች ምክር ቤት የፀደቁት ጉዳዮች ተግባራዊ መደረጋቸውን የመከታተልና የማረጋገጥ ኃላፊነት አለበት። በተጨማሪም መንግሥት በየዓመቱ የሃገሪቱን የበጀት ረቂቅ ያቀርባል።የሃገሪቱ ንጉሥ ዘወትር አርብ በየሣምንቱ ከመንግሥት ጋር ስብሰባ ያደርጋሉ። በዚህ ስብሰባ ላይ የካቢኔ ሚኒስትሮች የተለያዩ ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ለንጉሡ ያሳውቃሉ። እነዚህ ሳምንታዊ ስብሰባዎች የካቢኔ ስብሰባዎች ̋ ይባላሉ። የንጉሡ የፖለቲካ ሥልጣን በጣም አነስተኛ ቢሆንም እነዚህ ስብሰባዎች አስፈላጊ ናቸው።

በርካታ ፓርቲዎች ተጣምረው መንግሥት ሲመሰርቱ ጥምር መንግሥት ይባላል። መንግሥት የመሠረተው ፓርቲ ወይም ፓርቲዎች በጋራ ያላቸው የተወካዮች ምክር ቤት አባላት ቁጥር ከፍተኛ ከሆነ አብላጫውን የያዘ መንግሥት ይባላል። በሌላ በኩል መንግሥት የመሠረተው ፓርቲ ወይም ፓርቲዎች የምክር ቤት አባላት ቁጥር ዝቅተኛ ከሆነ አናሳ መንግሥት ይባላል።በቅርብ ዓመታት ኖርዌይ ውስጥ ሥልጣን የያዙ ሁሉም መንግሥታት ጥምር መንግሥታት ናቸው።

የሥልጣን ክፍፍል መርህ

የሥልጣን ክፍፍል መርህ ማለት የተወካዮች ምክር ቤት፣ መንግሥትና ፍርድ ቤቶች ሥልጣንን ይከፋፈላሉ ማለት ነው።

መረጃ

የስልጣን ክፍፍል መርህ

የስልጣን ክፍፍል መሰረቱ ያለውን ሥልጣን በሶስት ራሳቸውን በቻሉ የስልጣን ደረጃ ያከፋፍላል።

  • ህግ አውጪ ስልጣን፣ ህግ የምያፀድቀው ፓርላማው ነው።
  • ህግ አስፈጻሚ አካል፣ መንግስት ህጎችን ማቅረብና ሥራ ላይ መዋላቸውን ይቆጣጠራል።
  • ፍርድ ሰጪ አካል፣ ፍርድ ቤቶች ጉዳዮችን መርምሮ ፍርድ ይሰጣል።