ዲሞክራሲና የማህበራዊ ዋስትና ሥርዓት

ኖርዌይ በአለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ ትካፈላለች

ኖርዌይ የበርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አባል ሃገር ናት። ከእነዚህም ውስጥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)፣ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) እና የአዉሮፓ ኢኮኖሚያዊ ቀጠና ይገኙበታል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ)

FN-flagget

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኦክቶበር 24፣ 1945 የተመሰረተ ዓለም አቀፍ ድርጅት ነው። ይህ ድርጅት ለዓለም አቀፍ ሰላምና ደህንነት የሚሰራ ሲሆን፣ በዓለም ላይ ላሉ ሃገሮች የውይይት መድረክ በመሆን ያገለግላል። በአሁኑ ወቅት ተመድ 193 አባል ሃገራት አሉት።

በተጨማሪም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዓለም አቀፍ ህጐች፣ በኢኮኖሚ ዕድገትና በሰብዓዊ መብቶች ዙሪያ አስተዋፅኦ ያደርጋል። ድርጅቱ በሠላም ማስከበርም ከፍተኛ ሚና አለው።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሚተዳደረው ከአባል ሃገራት በሚያገኘው የገንዘብ ድጋፍ ነው።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተጨባጭ ህጋዊ ሥልጣን የለውም። ስለዚህ በድርጅቱ የሚወሰኑ ውሳኔዎች በአባል ሃገራት ላይ በህግ የፀኑ አይደሉም።

የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን (ኔቶ)

NATO-landene (Kilde: Wikimedia Commons)የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) 28 የአውሮፓና ሰሜን አሜሪካ አባል ሃገሮችን የያዘ የመከላከያ ድርጅት ነው። ኔቶ የተመሰረተው በ1949 ነው። አንድ ወይም ከዚያ በላይ የኔቶ አባል ሃገሮች በሌላ ሃገር ከተወረሩ ሁሉም የኔቶ አባል ሃገሮች በጋራ ለመተጋገዝና ለመዋጋት ቃል ኪዳን አላቸው።

የአውሮፓ ኢኮኖሚያዊ ቀጠና

ኖርዌይ የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገር አይደለችም። ይሁን እንጂ ሃገሪቱ አስገዳጅ በሆነ የአውሮፓውያን የትብብር ስምምነት ውስጥ አለችበት። ይህ ስምምነት የአውሮፓ ኢኮኖሚያዊ ቀጠና ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ስምምነቱን በፈረሙ ሃገሮች መካከል ያለውን ንግድና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ግንኙነቶችን ይወስናል። የሸቀጣ ሸቀጦች፣ የአገልግሎቶች፣ የሰው ኃይልና የካፒታል ዝውውርን በተመለከተ የወጡ የአውሮፓ ህብረት ህጐችን የአውሮፓ ኢኮኖሚያዊ ቀጠና ያከብራል። ኖርዌይ የአውሮፓ ህብረትን እንድትቀላቀል ኖርዌይ ውስጥ ሁለት ጊዜ (በ1972ና በ1994) ህዝበ ውሳኔ ምርጫ ተደርገው ነበር። ነገር ግን ሁለቱንም ጊዜ አብዛኛው ህዝብ ኖርዌይ የአውሮፓ ህብረት አባል መሆን የለባትም በማለት ድምፅ ሰጠ።

EU- og EØS-området (Kilde: Wikicommons)ሰማያዊ ቀለም ያለባቸው ሃገሮች የአውሮፓ ህብረት አባል ናቸው። ኖርዌይ፣ አይስላንድና ሊችተንስታይን (በአረንጓዴ ቀለም የተመለከቱ ሃገሮች) እና የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት ሁሉም የአውሮፓ ኢኮኖሚያዊ ቀጠና አባል ናቸው፡

የሸንገን ስምምነት

የሸንገን ስምምነት ዉጫዊ የድንበር ቁጥጥር ባላቸው አባል ሃገራት መካከል የድንበር ቁጥጥርን ለመተካት የአውሮፓ ሃገሮች የተፈራረሙት ስምምነት ነው። በሌላ አገላለፅ የሸንገን አገሮች እንደ አንድ ትልቅ ሥፍራ ስለሚታዩ ህጋዊ ፓስፖርት ወይም ቪዛ ሳይይዙ መግባት አይቻልም። አንድ ሰው የሸንገን ክልል ከገባ በኋላ ግን ያለምንም መደበኛ የፓስፖርት ቁጥጥር ወደ ሌሎች አባል ሃገሮች በነፃነት መንቀሳቀስ ይችላል። (ይህ ግን በአንዳንድ አጋጣሚዎች ሊቀየር ስለሚችል ከሃገር ውጭ ሲጓዙ ሁሌም ፓስፖርት መያዝን የኖርዌይ ፖሊስ ይመክራል።)ይህ ስምምነት የተፈረመው በ1985 በሉክሰምበርግ ሃገር በሸንገን ከተማ ነው። ዛሬ 27 የአውሮፓ ሃገሮች የዚህ ስምምነት አባል ናቸው።

የሸንገን ስምምነት የፈረሙ ሃገሮች፡ Schengen-området (Kilde: Wikicommons)