ኢኮኖሚ
ከዝቅተኛው የግብር ነጻ ተቀናሽ በላይ ገቢ ያላቸው ሠራተኞች በሙሉ ግብር ይከፍላሉ። አብዛኛው ከግብር የሚገኝ ገንዘብ ሠራተኞቹ ለሚኖሩበት ወረዳ ገቢ የሚደረግ ሲሆን፣ የተወሰነው ደግሞ ለመንግሥት ገቢ ይሆናል። አረጋዊያን ጡረተኞችና የሥራ አጥነት አበል እንዲሁም ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች የሚያገኙ ሰዎች ሁሉ ግብር ይከፍላሉ። ትልልቅ ድርጅቶች ግብር የሚፍሉት ለመንግሥት ነው።
ከምንሸምታቸው ሁሉም ሸቀጦችና ከምንጠቀምባቸው አገልግሎቶችም ለመንግሥት ታክስ እንከፍላለን። ይህ የቀረጥ ዓይነት የተጨማሪ እሴት ታክስ ይባላል። መደበኛው የተጨማሪ እሴት ታክስ መጠን 25 በመቶ ሲሆን በምግብ ምርቶች ላይ ግን 15 በመቶ ነው። ይህም ማለት እርስዎ አንድ ሸቀጥ ለመግዛት ከሚከፍሉት ውስጥ መንግሥት የሚያገኘው ታክስ አለ ማለት ነው። የተጨማሪ እሴት ታክስ ለመንግሥት በጣም አስፈላጊ የገቢ ምንጭ ነው። መንግሥት ከሚያገኘው ጠቅላላ የታክስ ገቢ ውስጥ 20 ከመቶ በላይ የሚኘው ከተጨማሪ እሴት ታክስ ነው።
የኖርዌይ ማህበራዊ ዋስትና ሥርዓት በአግባቡ መሥራት እንዲችል አንዱ ቅድመ ሁኔታ አብዛኛው ነዋሪ ሥራ እንዲይዝና የበኩሉን ድርሻ በታክስ አማካይነት አስተዋፅኦ እንዲያደርግ ማስቻል ነው። መንግሥት የሚያገኘው የገቢ መጠን ከወጪው የበለጠ መሆን አለበት።
የኖርዌይ ህብረተሰብ ከሚያኘው ማህበራዊ ዋስትና ጥቅማ ጥቅሞች የተወሰነውን ለምሳሌ የሆስፒታሎችን አገልግሎት መሸፈን የመንግሥት ኃላፊነት ነው። ይሁን እንጂ አብዛኛዎቹን ጥቅማ ጥቅሞች በገንዘብ የመደጐም ኃላፊነት ያለባቸው ወረዳዎች ነው።