ልጅና ቤተሰብ

የልጆች አስተዳደግ

Barn og foreldre

ልጆች በወላጆቻቸው ላይ ጥገኞች ስለሆኑ ወላጆች ልጆችን የማሳደግ ተቀዳሚ ኃላፊነት አለባቸው። በድሮ ጊዜ ልጆች ይታዩ የበረው እንደ ትናንሽ አዋቂዎች ̋̋ በመሆኑ ለቤተሰቦቻቸው ገቢ አስተዋጽዖ ለማድረግ ሥራ መሥራት ይጠበቅባቸው ነበር። ከዚህ በፊት ከብዙየ ቤተሰብ አባላት ጋር አብሮ መኖር የተለመደ ቢሆንም አሁን ግን አብዛኛዎቹ ልጆች የሚያድጉት ከእናትና ከአባታቸው እንዲሁም እህት ወንድሞቻቸው ጋር ነው። በርካታ ልጆች መዋዕለ-ህፃናት የሚገቡ ሲሆን ሁሉም ልጆች ከስድስት ዓመታቸው ጀምሮ ትምህርት ቤት ገብተው ይማራሉ።

በልጆች አስተዳደግ ላይ ያለው አመለካከት ቀድሞ ከነበረው ተቀይሯል። ዛሬ የህፃንነት ጊዜ የጫወታና የመማሪያ ጊዜ በመሆኑ እንደከዚህ በፊቱ ከልጆች ብዙ ነገር አይጠበቅም። ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ብዙ ጊዜ ማሳለፍ እንዲሁም አብረዋቸው በማይሆኑበት ጊዜ በልጆቻቸው ህይወት ውስጥ ምን እየተከሰተ እንደሆነ በተቻላቸው መጠን ማወቅ ይፈልጋሉ። ስለዚህ ከመዋዕለ-ህፃናት እና ከትምህርት ቤቶች ጋር ጥሩ ትብብር እንዲኖራቸው ማድረጉ ላይ በጣም ያተኩራሉ። አብዛኛዎቹ ወላጆች የልጆቻቸው ጓደኞች እና የጓደኞቻቸው ወላጆች እነማን እንደሆኑ ማወቅ አስፈላጊ መሆኑን ያምኑበታል።

ልጆች ከቤታቸው ውጭና ከአካባቢያቸው በርካታ ነገሮችን የሚማሩና የሚለማመዱ በመሆኑ የሚኖሩበት ማህበረሰብ እና አካባቢም ልጆቹ ህይወት ላይ የሚጫወቱት ሚና ይኖራል። የትኛውም ወላጅ የልጆቹን ዕድገት ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር አይችልም። በተጨማሪም የትኛውም ልጅ የቤተሰቦቹ ትክክለኛ ግልባጭ ሊሆን አይችልም። በአጠቃላይ ወላጆች ለልጆቻቸው ጥሩ ተምሳሌት በመሆን ልጆቻቸው በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ እንዴት መልካም ምግባር ማሳየትና ምላሽ መስጠት እንዳለባቸው አርዓያ ይሆናሉ።

ለብዙ ወላጆች ልጆችን ማሳደግ አንዳንድ ጊዜ ከብዶ ሊታያቸው ይችላል። ይህ ሲሆን ለምሳሌ የተሸለ ዕዉቀት ካለዉ ሰዉ ምክር መጠየቅ፤ በጉዳዩ ላይ የተፃፉ መፃህፍት ማንበብ ወይም መረጃዎችን ከድረ-ገፅ ማግኘት ይቻላል።