ልጅና ቤተሰብ

እኩልነት

Likestilling
እያንዳንዱ ቤተሰብ የህይወቱን መስመርና የሥራ ድርሻው እንዴት መሆን እንዳለበት ውሳኔው የራሱ ነው። ሆኖም የጾታ እኩልነት እና የሰው ልጅ እኩል ክቡርነት ሀሳብ በህጐችና በመብቶች ውስጥ እናገኛለን። ኖርዌይ ውስጥ የሚኖር ማንኛውም ሰው እነዚህን ህጐች ማክበር አለበት። ከህጐቹ ውስጥ የእኩልነት ህግ፣ የጋብቻ ህግ እና የውርስ ህግ ይገኙበታል።

ከኖርዌይ ህብረተሰብ ዋነኛ እሴቶች ውስጥ አንዱ ለሰዎች በሙሉ እኩል ክብር መስጠት ነው። ይህም ማለት በፆታ፣ በዕድሜ፣ በችሎታ፣ በባህላዊ አመጣጥ፣ በዘር ወይም በፆታዊ ግንኙነት ምርጫ ምክንያት ምንም ልዩነት ሳይደረግ ሁሉም ሰው እኩል ክብረት አለው። እያንዳንዱ ሰው እንደ ችሎታው መጠን እኩል ዕድሎችን እንዲያገኝ ህብረተሰቡ ጠንክሮ ይሰራል። ለዚህም ተጠቃሽ ከሚሆኑ ምሳሌዎች ውስጥ፡- ለአካል ጉዳተኞች በየትምህርት ቤቱ የሚሰጡ ልዩ ድጋፎች፣ ለፍልሰተኞች የሚሰጥ የኖርዌይኛ ቋንቋ ትምህርት፣ ለአንድ ዓይነት ሥራዎች አንድ ዓይነት ክፍያ ማድረግ የመሳሰሉት ናቸው።

የፆታ እኩልነትን በተመለከተ ባለፉት ጥቂት አሥርታት ዓመታት ውስጥ ብዙ ለውጦች ተከስተዋል። በሴቶችና በወንዶች የሥራ ድርሻ እና በቤትም ሆነ በማህበረሰቡ ውስጥ በሚሰጣቸው ሥፍራ ላይ የአስተሳሰብ ለውጥ ታይቷል።

Likestilling i arbeidslivet Likestilling i hjemmet

በ197ዐዎቹ የሴቶች መብቶች በህብረተሰቡ ውስጥ እንዲከበሩና ከወንዶች እኩል የትምህርትና የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ለጉዳዩ የሚሰጠው ትኩረት እየጨመረ ነው። በመሆኑም የሴቶች በሥራ ዘርፍ የመሰማራት መጠን ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ ዛሬ ቁጥራቸው ከወንዶች ቁጥር የሚቀራረብ ሴቶች ሥራ አላቸው። ይሁን እንጂ አሁንም የተለምዶ የወንድና የሴት ሙያዎች እንዳሉ ሲሆን፣ ከወንዶች ይልቅ ብዙ ሴቶች የከፊል ሰዓት ሥራ ይሰራሉ። በአሁን ጊዜ ከወንዶች ጋር ተቀራራቢ ቁጥር ያላቸው ሴቶች በከፍተኛ ደረጃ እየተማሩ ቢሆንም አብዛኛዎቹ ሙያ የሚመርጡት ልማዳዊ በሆነ መልኩ ነው። ሴቶች በአብዛኛው በጤና እንክብካቤ እና በትምህርት ዘርፎች ሲሰለጥኑ ወንዶች ደግሞ ይበልጥ ወደ ቴክኖሎጂና ሳይንስ ያመዝናሉ። ምንም እንኳን ሥራ ላይ ከተሰማሩ ሰዎች ውስጥ ግማሽ የሚጠጉት ሴቶች ቢሆኑም በሥራዉ ዓለም ሁለት ሶስተኛውን የበላይ ኃላፊነት ቦታ የያዙት ወንዶች ናቸው።

ዛሬ በአብዛኛው ቤተሰቦች ዉስጥ በተለይም በወጣት ቤተሰቦች ውስጥ ወንዶችና ሴቶች የቤት ውስጥ ሥራዎችን እንዲሁም ልጅ የማሳደግ ሥራን ተከፋፍሎ መሥራት የተለመደ ነው። ይሁን እንጂ የቤት ውስጥ ሥራ አሁንም ከወንዶች ይልቅ ሴቶች ብዙ ጊዜያቸውን ይጠቀማሉ።

መረጃ

የእኩልነት ህግ

የእኩልነት ህግ የተደነገገው እኩልነት እንዲሰፍንና በተለይም የሴቶች መብት እንዲከበር ተብሎ ነው። የህጉ ዓለማ ለሴቶችና ለወንዶች እኩል የመማር፣ የመሥራትና የባህል እንዲሁም የሙያ እድገት እድል እንድያገኙ ነው። ህጉም ሁሉም መንግስታዊ ባለሥልጣናት በየትኛውም የህብረተሰብ ክፍል በፆታ መካከል እኩልነት እንዲኖር ጠንክረው እንዲሰሩ ያስገድዳቸዋል።