ልጅና ቤተሰብ

በጋብቻ ውስጥ ያሉ መብቶችና ግድታዎች

Brudepar

ከጋብቻ ድንጋጌ የተቀነጨበ፡-

  • ማንኛውም ሰው ዕድሜው ከ18 ዓመት በላይ ሆኖ ትዳር ከሌለውና ኖርዌይ ውስጥ በህጋዊ የሚኖር ከሆነ ጋብቻ መፈፀም ይችላል።
  • ሁሉም ጋብቻ የሚፈፀመዉ በተጋቢዎች ነፃ ምርጫ መሆን አለበት። ወንዶችና ሴቶች የትዳር አጋራቸውን በነፃነት የመምረጥ እኩል መብት አላቸው። የሃገሪቱ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ እንዳስቀመጠው ጥቃትን በመጠቀም፣ ነፃነትን በመንፈግ፣ በጫና ወይም በማስፈራራት ጋብቻ የሚፈፅም ማንኛውም ሰው እስከ ስድስት ዓመት በእስራት ሊቀጣ ይችላል። በዚህ ወንጀል ተባባሪ ሆኖ መገኘት ተመሳሳይ ቅጣት ያስከትላል።
  • ከተጋቢዎች ውስጥ አንደኛው ሰው በትዳር አብሮ ለመቆየት ካልፈለገ ለመለያየት ጥያቄ ማቅረብ ይችላል። ጥንዶቹ ለአንድ ዓመት ተለያይተው ከቆዩ በኋላ መፋታት ይችላሉ። ለመለያየት ጥያቄ ሳያቀርቡ ጥንዶቹ ለሁለት ዓመታት አብረው ካልኖሩ መፋታት ይችላሉ። ወንዶችና ሴቶች እኩል የመለያየት ጥያቄ የማቅረብ እና ፍቺ የማመልከት መብት አላቸው።
  • ባል ወይም ሚስት በአንዳቸው ላይ ወይም በልጆቻቸው ላይ የመግደል ሙከራ፣ ጥቃት፣ ከፍተኛ ስቃይ ቢያደርሱ ወይም እነዚህን የሚመለከት የፍርሃት ስሜት ቢፈጠር ተጠቂው ሰው ያለምንም የመለያየት ጥያቄ ፍቺ መጠየቅ ይችላል። ጋብቻው የተፈፀመው በማስገደድ ከሆነም የተገደደው ሰው ፍቺ መጠየቅ ይችላል። አንድ ተጋቢ በነዚህ ምክንያቶች ትዳሩን ለቆ ቢወጣ ከመኖርያ ፍቃድ ጋር በተያያዘም መብቶች ይኖሩታል።
  • ጋብቻ ውስጥ ምን የማን ነው? አንድ ሰው ከማግባቱ በፊት የነበረው ማንኛውም ንብረት ከጋብቻ በኋላም የራሱ ንብረት ነው። በተጨማሪም ከጋብቻ በኋላ የሚገኙ ሁሉም የውርስ ንብረቶችና ስጦታዎች እንዲሁም በግል የተገዙ ነገሮች የግለሰቡ የግል ንብረቶች ናቸው። ስለዚህ የትዳር አጋር ፈቃድ ሳያስፈልግ እነዚህን ንብረቶች መሸጥ ወይም ለሌላ አሳልፎ መስጠት ይቻላል። ነገር ግን ጥንዶቹ በጋራ የገዟቸው ወይም ለቤታቸው የገዙት ማንኛውም ነገር የጋራ ንብረት ነው።

መረጃ

የጋብቻ ህግ

የጋብቻ ህግ በጋብቻ ጊዜ ያለውን ሁኔታ ይደነግጋል። ሳይጋቡ አብረው የሚኖሩት የተጋቡትን ያህል አንዱ በሌላው ላይ ግዴታና መብት አይኖረውም። እናም ሳይጋቡ አብረው የሚኖሩት የራሱ የሆነ ውል ሊፈራረሙ ይገባል።