ጤና

ጤናና የመኖር ዋስትና

ለጤናችን ኃላፊነት የሚወስደው ማነው?

ከዚህ በፊት ለሁሉም ህመምተኞች ጤና ኃላፊነት የሚወስደው ብሔራዊ የጤና አገልግሎት እንደሆነ ይታሰብ ነበር።

ከቅርብ አመታት በኋላ ለጤናችን ትልቁን ኃላፊነት መውሰድ ያለብን ራሳችን መሆናችንን ማሰብ የተለመደ ሆኗል። የምንመርጠዉ የአኗኗር ዜይቤ ጤናችን ላይ ተፅዕኖ አለው። የጤና ተቋማት ስለጤናችን ምክርና መመሪያ የመስጠት ኃላፊነት ቢኖርባቸውም ምክራቸውን ተግባራዊ ማድረግ ግን የራሳችን ኃላፊነት ነው። የተለያዩ በሽታዎችን እንዴት አስቀድሞ መከላከልና በምን መንገድ መታከም እንዳለብን መረጃዎችን በቀላሉ ማግኘት እንችላለን። በድረ-ገፆች ላይ ከምናገኘው መረጃ በተጨማሪ ለምሳሌ ከሐኪም ቤትና ከፋርማሲዎች በራሪ ወረቀቶችን ማግኘት ይቻላል። በጤና ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በርካታ መረጃዎችና ትምህርቶች ይሰጣሉ። በትምህርት ቤቶች ውስጥ ጤና አንድ ዓቢይ ርዕሰ-ጉዳይ ሲሆን፣ መንግሥት የተለያዩ የጤና መረጃዎችን የማሰራጨት ዘመቻዎች ያደርጋል። ቴሌቪዥንና ሬዲዮም ብዙ ጤና ነክ መርሀ ግብሮች አሏቸዉ።

.

ምንም እንኳን የሃገሪቱ የማህበራዊ ዋስትና ሥርዓት ዜጐች የተሻለ ጤና እንዲኖራቸው የመሥራት ብዙ ኃላፊነት ቢኖርበትም የራስን ጤና በተቻለ መጠን መንከባከብ የእያንዳንዱ ሰው ድርሻ ነው፡ በብዙ ሃገሮች የሚገኙ ህመምተኞች ለህመማቸው መውሰድ ያለባቸውን ህክምና የመጨረሻ ውሳኔ መስጠት ያለባቸው ሐኪሞች እንደሆኑ ያምናሉ። በተጨማሪም ከሐኪም የመድኃኒት ማዘዣ ሳይይዙ አለመውጣት የተለመደ ነው። ኖርዌይ ውስጥ ግን ታካሚውና ሃኪሙ መደረግ ስለሚገባቸው የህክምና እና ክትትል አማራጮች ውይይት ያደርጋሉ።

መልካም ጤንነት ማለት ከህመም አለመኖር በላይ ነውን?

ለአንዳንድ ሰዎች መልካም ጤንነት ማለት አለመታመም ነዉ ይላሉ። ለሌሎች ደግሞ መልካም ጤንነት ማለት የተስተካከለና ምቹ ህይወት መምራት ነው ይላሉ።

ሁለቱም ለመልካም ጤንነት የተሰጡ ትርጉሞች ትክክል ናቸው። ከባድ በሽታዎች በሚበዙበትና ድህነት የዕለት ተዕለት ኑሮ በሆነባቸው ህብረተሰቦች ውስጥ ምናልባት የመጀመሪያው የጤና ትርጉም በጣም የተለመደ ነው። ለብዙ በሽታዎች መድሃኒትና ህክምና ማግኘት በሚቻልባቸው ሌሎች ሃገሮች ውስጥ ደግሞ መልካም ጤና ማለት የአካላዊና የአዕምሮአዊ ጤንነት መኖር ብቻ ሳይሆን ከዚያ በላይ ነው።

መረጃ

የኢኮኖሚ ድጋፎች

በመደጋገፍ ላይ በተመሰረተ ህብረተሰብ ውስጥ ዋና ዓላማው ሁሉም ሰው የተቻለውን ያህል ጥሩ ህይወት እንዲኖር ነው። ይህ ደግሞ ጥሩ ጤንነትንም ጨምሮ ነው።

ህዝብን የሚደግፍ መንግስት ሁሉም ዜጋ የጤና አገልግሎት፣ ከኢኮኖሚ አቅም አኳያ ሳይሆን ሁሉም ሰው የሚገባውን ህክምና እንድያገኝ ሃላፊነት ይወስዳል። ስለዚህም ይህንን ለሟሟላት የተለያዩ የኢኮኖሚ ድጋፎች አሉ።

ሚስጢርን የመጠበቅ ግዴታ

ሁሉም በጤና መስክ የሚሰሩ ሰራተኞች ሚስጢርን የመጠበቅ ግዴታ አለባቸው። ይህም ማለት በሽተኛ ሳይፈቅድ ለማንም ሰው ስለሱ መንገር አይቻልም።