ልጆችና ጤና
የቅድመ-ወሊድ ክትትል እና ወሊድ
በአንድ ሀገር ያለ የኑሮ ደረጃ፣ የጤና አገልግሎት፣ የህክምና ዕድገት ማህበራዊ ደህንነትና ሌሎች ለወላጆችና ለልጆች የሚደረጉ ማህበራዊ ዋስትና ጥቅማ ጥቅሞች በአንድ ህብረተሰብ ውስጥ ለሚከሰት የጨቅላ ህፃናት የሞት መጠን ላይ አስተዋጽዖ አላቸው። በአሁኑ ወቅት በኖርዌይ የጨቅላ ህፃናት ሞት መጠን ከሌሎች ሃገሮችና ካለፉት ጊዜያት አንፃር ሲታይ ዝቅተኛ ነው። ኖርዌይ ውስጥ ነፍሰ ጡር ሴቶች ነፃ የቅድመ ወሊድ ክትትል የማግኘት መብት አላቸው። ክትትሎቹ የሚደረጉት በመንግሥት የጤና ተቋማት ወይም በግል ሐኪሞች አማካይነት ነው። ክትትሎቹ በፈቃደኝነት የሚደረጉ ሲሆን ዓላማቸውም የእናትና የልጅ ጤናን በእርግዝና ወቅት፣ በወሊድ ጊዜና በድህረ-ወሊድ ጊዜ ለመንከባከብ ነው። ኖርዌይ ውስጥ አንድ ነፍሰጡር ሴት ከስምንት እስከ አሥራ ሁለት የሚደርስ የህክምና ክትትል እንድታደርግ ትመከራለች። ብዙ ሴቶች የሚወልዱት በሆስፒታል ሲሆን፣ የወሊድ አገልግሎቱ ደግሞ በነፃ ነው።
ኖርዌይ ውስጥ የሚኖሩ ሁሉም ልጆችና ወጣቶች በየጊዜው የጤና ክትትል እንዲያደርጉ ይጋበዛሉ። ህፃናት ከጨቅላ እድሜ ጀምሮ ትምህርት ቤት እስኪገቡ ድረስ ይህንን አገልግሎት የሚያገኙት በመንግሥት የጤና ተቋማት ውስጥ ነው። ህፃናት ትምህርት ከጀመሩ በኋላ ግን በትምህርት ቤት የሚገኙ የጤና አገልግሎቶች ክትትል ያደርጉላቸዋል። ለወጣቶችና ለአዋቂዎችም አገልግሎት የሚሰጡ የጤና ተቋማት በብዙዎቹ ወረዳዎች (ኮሚዩነ) ውስጥ አሉ። በመንግሥት የጤና ጣቢያዎች እና በትምህርት ቤት የጤና አገልግሎቶች የሚሰጡ የጤና እንክብካቤዎች ሁሉ በነፃ ናቸው።
ጤና ጣቢያው የህፃኑን ዕድገት በመመርመር ህፃኑ በተገቢው መጠን እያደገ መሆኑን፣ የህፃኑ የማየትና የመስማት ሁኔታ ጤናማ መሆኑን እንዲሁም ህፃኑ በትክክል መረዳትና መናገር መማሩን ይከታተላል። በህፃኑ ዕድገት ላይ ችግሮች ካጋጠሙ እነዚህ የጤና ጣቢያው አስፈላጊውን እርዳታና መምር ይሰጣል።
በተጨማሪም ኖርዌይ ውስጥ የሚኖሩ ሁሉንም ልጆችንና ወጣቶችን ከአደገኛ በሽታዎች ለመከላከል ክትባቶች ይሰጧቸዋል። እነዚህ ክትባቶች በቀላሉ፣ በቀልጣፋና ጉዳት በማያስከትል መንገድ በሽታዎችን ይከላከላሉ። ክትባት የሚሰጠው በፈቃደኝነት ቢሆንም ሁሉም ወላጆች ልጆቻቸውን እንዲያስከትቡ የኖርዌይ የመንግሥት አካላት በጥብቅ ይመክራሉ።
በሽታን ለመከላከል የሚሰጡ ክትባቶች በነፃ ናቸው። ነገር ግን ተጨማሪ ክትባቶች ለምሳሌ የውጭ ሃገር ጉዞ ጋር በተያያዘ ለሚደረጉ ክትባቶች ወጪ ተጠቃሚው ራሱ መክፈል ይኖርበታል።