ጤና

የአእምሮ ጤና

የአዕምሮ ጤና ችግር ሁሉም ሰዉ በህይወቱ በሆነ ወቅት ሊከሰት ይችላል። የአዕምሮ ጤና ችግር የሚያስከትሉ በርካታ ምክንያቶች አሉ። በህይወት ውስጥ የሚያጋጥም አስቸጋሪ ሁኔታ ለምሳሌ የቤተሰብ ችግሮች ወይም አስቸጋሪ የሥራ ሁኔታ የአዕምሮ ጤና ችግሮችን ሊያስከትል ይችላል። አንዳንድ ጊዜ የአዕምሮ ሕመሞች የሚከሰቱት ከአስጊ ችግሮች፣ ሞት፣ ድንገተኛ አደጋዎች ወይም በጦርነት ሁኔታዎች በተፈጠሩ አጋጣሚዎች ካለፉ በኃላ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ውስጣቸው በዘር የወረሱት በቀላሉ በአእምሮ ህመም የመያዝ ችግር ሲኖርባቸው ህመሙን ጭንቀት ሊቀሰቅሰው ይችላል።

የአዕምሮ ጤና ላይ ያለው አመለካከት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀየረ መጥቷል። ዛሬ ኖርዌይ ውስጥ አብዛኛዎቹ ሰዎች ለአዕምሮ ህመም ጥሩ የመረዳት አመለካከት አላቸው። የአዕምሮ ህመም ያለባቸው ሰዎች ልክ አካላዊ ህመም እንዳለባቸው ሰዎች ሁሉ ከመንግሥት የጤና ጥበቃ አገልግሎት ህክምና እና ድጋፍ ማግኘት እንዳለባቸው ብዙ ሰዎች ያምናሉ። በተጨማሪም የአዕምሮ ህመም በህክምና ሊድን እንደሚችል የአብዛኛው እምነት ነው።

የስደተኝነት ሕይወት ሂደት

ወደ ሌላ ሃገር ለመኖር የሚሄዱ አብዛኛዎቹ ሰዎች በሚከተለው ስነ-ልቦናዊ የስደተኝነት የሕይወት ሂደት ውስጥ ያልፋሉ። በመጀመሪያዎቹ ወቅቶች ነገሮች ሁሉ መልካም መስለው ስለሚታዩዋቸዉ ስለ አዲሷ ሃገር ጥሩ ስሜት ይኖራቸዋል። ከጊዜ በኋላ ግን ብዙዎቹ የዱባቴ ስሜት ያድርባቸውና አዲስ ስለሚኖሩበት ሃገር ብዙ አሉታዊ ነገሮችን ማሰብ ይጀምራሉ። አብዛኛዎቹ ሰዎች ቀስ በቀስ የህይወት መረጋጋትን ያገኛሉ።