የስራ ህይወት

ስራና የህዝብ አገልግሎት ዋስትና

ብዙ ሰዎች ሥራ አግኝተው ደሞዝ የሚከፈላቸው ከሆነ መንግሥትና ወረዳዎች (ኮሚዩነ) ከፍተኛ የግብር/ታክስ ገቢ ይኖራቸዋል ማለት ነው። ይህ ደግሞ ለህብረተሰቡ በርካታ ጥቅሞች ይሰጣል።

  • ለትምህርት ቤቶች፣ የጤና ተቋማት፣ ለመንገድ ግንባታ ወዘተ ብዙ የገንዘብ ድጋፍ ያስገኛል።
  • የማህበራዊ ዋስትና ጥቅማ ጥቅሞችን ለመስጠት ብዙ ግብዓት ይኖራል።
  • የመንግሥት ወጪ ይቀንሳል (የሥራ አጥነት አበል፣ የማህበራዊ ድጋፍ ወጪ፣ የማህበራዊ ዋስትና ጥቅማ ጥቅሞች ወዘተ. ይቀንሳሉ።)

ከ1960ዎቹ መጨረሻ ጀምሮ ኖርዌይ የነዳጅ አምራች ሃገር ሆናለች። የነዳጅ ሃገር የሚባሉት የነዳጅ ምርት ዋነኛ የገቢ ምንጭ የሆነባቸው ሃገሮች ናቸው።

የኖርዌይ መንግሥት የነዳጅ ዘይትና ጋዝ ወደ ውጭ በመላክ ከፍተኛ ገንዘብ ያገኛል። ኖርዌይ የማህበራዊ ዋስትና ሥርዓት መከተል የቻለችው ከነዳጅ ከምታገኘው ገቢ እንደሆነ ብዙዎች ያምናሉ። ይህ ግን እውነት ነው?

ከነዳጅ ዘይትና ጋዝ ምርት የሚገኘው ገቢ ለማህበራዊ ዋስትና ሥርዓት እገዛ ያደርጋል። ከመንግሥት ወጪ አንድ-አራተኛ የሚሆነው የሚሸፈነው በዚሁ ገቢ ነው። ግብር እንዲሁም ሌሎች ገቢዎች ቀሪውን ወጪ ይሸፍናሉ።

ሥራ ላይ በመሰማራታችን ተጠቃሚ የሚሆነው ማህበረሰቡ ብቻ አይደለም። ብዙ አዋቂዎችም ሥራ በማግኘታቸው በግላቸው ተጠቃሚ ናቸው።

ሥራ የሚከተሉትን ጥቅሞች ይሰጠናል፡-

  • ገንዘብ ያስገኝልናል።
  • ራስን ለመቻልና ትርጉም ያለው ህይወት ለመኖር ያስችላል።
  • በህብረተሰብ ውስጥ ያለንን ደረጃና ማህበራዊ ግንኙነት ያሳድጋል።
  • ችሎታችንንና ብቃታችንን ለመጠቀም ያስችለናል።
  • ለህብረተሰቡ አስተዋፅኦ እንድናደርግና የጠቃሚነት ስሜት እንዲኖረን ያደርጋል

መረጃ