የስራ ህይወት

ታሪካዊ እድገት

ከ150 ዓመታት በፊት ኖርዌይ ውስጥ ዋና ዋናዎቹ የሥራ ዘርፎች ግብርና፣ የደን ልማት እና አሳ ማጥመድ ነበሩ። ከዚያ ወዲህ ግን ብዙ ለውጦች ተከስተዋል። በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ ፋብሪካዎች ብቅ ብቅ ማለት ሲጀምሩ ብዙ ሰዎች በእነዚህ ፋብሪካዎች ውስጥ ተቀጥረው ለመሥራት ከገጠር ወደ ከተማ መጡ። በ20ኛው ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ ብዙ ቁጥር ያላቸው የኢንዱስትሪ ሥራዎች ተፈጠሩ። በተመሳሳይ ጊዜ ደግሞ በርካታ የኖርዌይ ዜጐች ወደ አሜሪካ በመሄድ ኑራቸውን እዚያ አደረጉ።

በ1950 ከኖርዌይ ህዝብ 20 በመቶ የሚሆነው በግብርና ሥራ ላይ የተሰማራ ነበር። አሁን ግን ይህ ቁጥር ከሦስት በመቶ በታች አሽቆልቁሏል። ይሁን እንጂ አሁን ኖርዌይ ውስጥ የሚመረተው የምግብ መጠን ከድሮው የበለጠ ነው። ለዚህ ዋነኛው ምክንያት ደግሞ ዛሬ ሥራን በቀላሉ ለመሥራት የሚያስችሉና ይበልጥ ውጤታማ የሚያደርጉ የእርሻ መሣሪያዎች መኖራቸው ነው።

ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ደግሞ በኖርዌይ የሰው ኃይል ገበያ ላይ መሠረታዊ ለውጦች ተከስተዋል። ከእነዚህም ውስጥ በኢንዱስትሪዎች ውስጥ ያለው የሥራ ቁጥር በእጅጉ መቀነስ ይገኝበታል።

በ1960ዎቹ መጨረሻ ላይ የነዳጅ ዘይት በሰሜን ባህር ከተገኘ ወዲህ የነዳጅ ዘይትና ጋዝ የኖርዌይ ኢንዱስትሪ ዋነኛ አካል ናቸዉ። የነዳጅ ዘይትና ጋዝ ለኖርዌይ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ጥቅም አላቸው። ምንም እንኳ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ወደፊት አረንጓዴ የኃይል ምርት ትኩረት የሚሰጠው ቢሆንም የነዳጅ ዘይትና ጋዝ ለኖርዌይ የሚሰጠው ጠቀሜታ አሁንም ይቀጥላል።

በአሁን ወቅት አብዛኞቹ ሰራተኞች ማለትም ወደ 1.8 ሚሊዮን የሚጠጉ የተሰማሩት በአገልግሎት ዘርፍ ነው። ስለዚህ ኖርዌይ ውስጥ ሥራ የሚፈልግ ማንኛውም ሰው በሱቆች፣ በጤና እንክብካቤ ተቋማት፣ በትምሀርት ቤቶች፣ በመዋዕለ ህፃናት ወይም በግል የመጓጓዣ ዘርፎች ሥራ የማግኘት ዕድሉ ከፍተኛ ነው። ከአዳዲስ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ጋር ተያያዥነት ባላቸው የሥራ ዘርፎች ውስጥም ብዙ የሥራ ዕድሎች ይገኛሉ።