ትምህርትና የሙያ ማረጋገጫ

አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት

Småskolebarn Ungdomsskoleelever

ስለአንደኛ መለስተኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ጥቂት መረጃዎች፡

  • ኖርዌይ ውስጥ ሁሉም ልጆች ለአሥር ዓመታት ያህል የሚቆይ የአንደኛ መለስተኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት የማግኘት መብት አላቸው። ህፃናት ስድስት ዓመት ሲሞላቸው አንደኛ ክፍል ገብተው መማር ይጀምራሉ።
  • ሁሉም ልጆች ለነሱ የተመቻቸ ትምህርት የማግኘት እና እንዲሁም ተጨማሪ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ደግሞ እገዛ የማግኘት መብት አላቸው።
  • የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች የቃልና የፅሑፍ ፈተና የሚወስዱ ቢሆንም ውጤት (ማርክ) ግን አይሰጣቸውም።
  • የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ለሁሉም የትምህርት ዓይነቶች ውጤት ይሰጣቸዋል። የውጤቱ ስኬል ከ1 እስከ 6 ሲሆን፣ 1 በጣም ዝቅተኛ ሲሆን 6 ደግሞ በጣም ከፍተኛ ነው።
  • ሁሉም የመጀመሪያ ደረጃ ተማሪዎች ወደሚቀጥለው የክፍል ደረጃ ይዛወራሉ። ተማሪዎች ከክፍል ክፍል ለመዛወር ውጤታቸው ከግምት ውስጥ አይገባም። ማንም ልጅ በአንድ የክፍል ደረጃ እንዲደግም አይደረግም።
  • የመጀመሪያ መለስተኛና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በመላ ሃገሪቱ ተመሳሳይ ሁኔታ የተደራጁ ናቸዉ። ለምሳሌ እያንዳንዱ ትምህርት ቤት በየዓመቱ 190 የትምህርት ቀናት ይኖሩታል፤ ነገር ግን የወረዳዉ ፖለቲከኞች ትምህርት ቤቶች ለእረፍትና ለበዓላት የሚዘጉባቸውን ቀናት ይወስናሉ።
  • ሁሉም ተማሪዎች በተመሳሳይ ሥርዓተ-ትምህርት (ካሪኩለም) ይማራሉ። ሥርዓተ-ትምህርቶቹ የሚፀድቁት በተወካዮች ምክር ቤት ነው። በመሆኑም ሃገሪቱ ውስጥ በማንኛውም ወረዳ የሚገኙ ተማሪዎች በሙሉ ተመሳሳይ ትምህርት ይሰጣቸዋል።
  • ከመንግሥት የመጀመሪያ መለስተኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በተጨማሪ የግል ትምህርት ቤቶችም አሉ። ወደ 2.5 በመቶ የሚሆኑት የኖርዌይ ልጆች በግል ትምህርት ቤቶች ይማራሉ።

የትምህርት እድል እኩልነት

ሁሉም ልጆች ያላቸው ችሎታና አቅም እንዳለ ሆኖ በየትምህርት ቤታቸው ተገቢውን ትምህርት የማግኘት መብት እንዳላቸው የሃገሪቱ የትምህርት አዋጅ ይደነግጋል። የዚህ መብት ፖለቲካዊ መርህ የትምህርት እድል እኩልነት ይባላል።

ለመጀመሪያ መለስተኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚደረግ የገንዘብ ድጋፍ

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት የሚሰጠው በነፃ ነው። ልጆች የመማሪያ መፃህፍትን ከትምህርት ቤት የሚዋሱ ሲሆን፣ ደብተሮች፣ እርሳሶች እና ሌሎች ቁሳቁሶችንም ከትምህርት ቤቱ ያገኛሉ።

ሁሉንም ወጪ የሚሸፍነው መንግሥት ነው። ከእነዚህ ወጪዎች ዋነኞቹ የመምህራን ደሞዝ፣ የግንባታና ከህንፃዎች ጋር የተያያዙ የዕለት ተዕለት ወጪዎች ናቸው።

ልጆቻቸውን በግል ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ ወላጆች የትምህርት ክፍያ ይከፍላሉ። ወላጆች የሚከፍሉት የተጠቃሚ የክፍያ ድርሻ ሲሆን ቀሪው በመንግሥት ይሸፈናል።

መረጃ

አሰፉ፣ ከትምህርት ትርፍ ጊዜ ማቆያ

ሁሉም ወረዳዎች ከትምህርት ትርፍ ጊዜ ማቆያ (አሰፉ) አገልግሎት ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች ያቀርባሉ
አሰፉ በፍላጎት ከትምህርት ሰዓት በፊት ወይም በኋላ ልጆች እንዲጠብቁላቸው እርዳታ ለሚፈልጉ ቤተሰቦች የሚሰጥ አገልግሎት ሲሆን ለምሳሌ ቤተሰብ ሥራ ላይ ሲሆን መጥቀስ ይቻላል። አሰፉ የትምህርት አገልግሎት አይደለም፣ ነገር ግን ልጆች ብዙውን ጊዜ በአሰፉ የቤት ሥራ ለመስራት እርዳታ ያገኛሉ።
ልጆችን ወደ አሰፉ መላክ በነፃ አይደለም። ቤተሰብ የተጠቃሚ ድርሻን በየወሩ የሚከፍል ሲሆን ቀሪውን መንግስት ይሸፍናል። የተጠቃሚዉ ድርሻ ክፍያ ከወረዳ ወረዳ ይለያያል። በአንዳንድ ወረዳዎች አነስተኛ ገቢ ያለዉ ቤተሰቦች ክፍያው እንዲቀነስላቸው ማመልከት የሚችሉ ሲሆን ሌሎች ወረዳዎች ውስጥ ደግሞ ሁሉም ተመሳሳይ ዋጋ ይከፍላሉ። አንዳንድ ወረዳዎች አንድ ቤተሰብ በአንድ አሰፉ ውስጥ ብዙ ልጆች ካሉት የክፍያ ቅናሽ ስያደርጉ ሌሎች ግን አያደርጉም።

ዲስፕሊን

መምህራን ተማሪዎችን መምታት አይፈቀድላቸውም። የትምህርት ቤት ዲስፕሊን የሚከበረዉ የልጆችን ሰብአዊ ክብር በጠበቀ ሁኔታ ነው። መምህራን ተማሪዎችን የሚያከብሩ ሲሆን ተማሪዎችም ለመምህራን አክሮት ይኖራቸዋል።