ታሪክ፣ ህብረተሰብና የኑሮ ሁኔታ

የኖርዌይ አገር አጭር ታሪክ

Vikingskip

የቪኪንግ ጊዜ

ከ800 እስከ 1100 አ.ም እ.ኤ.አ ከክርስቶስ ልደት በኋላ ያለው ጊዜ የቪኪንግ ጊዜ ይባላል። በቪኪንግ ጊዜ መጃመሪያ አካባቢ ኖርዌይ አገር አልነበረችም ነገር ግን በብዙ ትንንሽ የራሳቸው ንጉስ ባላቸው ሀገሮች የተዋቀረች ነበረች። በ872 አ.ም እ.ኤ.አ ቪኪንግ ሀራልድ ሆርፋርጌ ለመላው ኖርዌይ ሀገር ንጉስ ሆነ። ብዛት ያላቸው ቪኪንጎች ወደ ሌላ ሀገር ተጉዘዋል። አንዳንድ ቪኪንጎች ነጋዴ ስለነበሩ እቃዎችን በመግዛት ይሸጡ ነበር ሌሎቹ ደግሞ ጦረኞች ስለነበሩ ዘረፋና ግድያን ያካሂዱ ነበር። በዛሬው ጊዜ ስለ ቪኪንጎች ባወራን ቁጥር ስለ ጦረኞች እናስታውሳለን። በ1000 አ.ም እ.ኤ.አ የክርስትና ሃይማኖት ወደ ኖርዌይ ሀገር ገባ። ጥንታዊ የኖርዊጅያን ሀይማኖትም በክርስትና ሃይማኖት ተቀየረ። Borgund stavkirke

የዴንማርክና የኖርዌይ ሀገሮች ህብረት

በ1300 አ.ም እ.ኤ.አ የዴንማርክ ሀገር በኖርዌይ ሀገር ላይ የበለጠ ተፅኖ ማድረግ የቻለችና ከ1397 አ.ም እ.ኤ.አ ጀምሮ ኖርዌይ ከዴንማርክና ከስዊድን ሀገሮች ጋር ህብረት ፈጠረች። ይህም ህብረት ለሁሉም እኩል የሆነ አንድ ንጉስ ነበረው። ከጊዜ በሗላ ስዊድን ከህብረቱ ስትወጣ ህብረቱ በኖርዌይና በዴንማርክ መካከል እስከ 1814 አ.ም እ.ኤ.አ ቆይቷል። ፖለቲካዉ የሚመራዉ ከዴንማርክ ነበር። የህብረቱ የባህል ማዕከል ኮፐንሃገን ነበር። ኖርዊጂያን በዴንማርክ ቋንቋ ይፅፉና ያነቡ ነበር። የኖርዌይ ገበሬዎችም ለዴንማርክ ንጉስ ቀረጥ ይከፍሉ ነበር።

የዴንማርክና የኖርዌይ ሀገሮች ህብረት

Eidsvoll 1814 - © Stortingsarkivet/ foto: Teigens fotoatelier as

ኖርዌይ በሜይ 17፣ 1814 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) የራሷን ህገ-መንግሥት ያፀደቀችበት ዓመት በመሆኑ በሃገሪቱ ታሪክ በልዩ የሚታወስ ዓመት ነው። በ1800ዎቹ መጀመርያ አውሮፓ ውስጥ ብዙ ጦርነቶች ነበሩ። ከእነዚህም ውስጥ በእንግሊዝና በፈረንሳይ መካከል የተደረገው ጦርነት አንዱ ነው። በዚህ ጦርነት የዴንማርክ እና ኖርዌይ ጥምረት ፈረንሳይን በመደገፍ ሲሰለፍ ሲዊዲን ደግሞ ለእንግሊዝ ወግና ተዋግታለች። በጦርነቱ ፈረንሳይ ስትሸነፍ የዴንማርኩ ንጉሥ ኖርዌይን ለሲዊድን ለመስጠት ተገደዱ።

የዴንማርክና የኖርዌይ ውህደት በ1814 ዓ.ም ሲፈርስ ኖርዌያውያን ሃገራቸው ነፃ ትወጣለች የሚል ተስፋ ነበራቸው። በመሆኑም ከሃገሪቱ ደቡባዊ ክፍል የመጡ 112 ግንባር ቀደም ሰዎች አከርሽሁስ አውራጃ ውስጥ የምትገኝ አይድስቮል በምትባል ሥፍራ በመሰባሰብ ነፃነቷን የተቀዳጀች ኖርዌይ የምትመራበትን ህገ-መንግሥት አረቀቁ። ይሁን እንጂ ኖርዌይ ከሲዊድን ጋር ለመዋሃድ ተገደደች፤ ውህደቱም በህዳር ወር 1814 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) እውን ሆነ። ከሲዊድን ጋር የተመሰረተው ውህደት ግን ቀድሞ ከዴንማርክ ጋር ከነበረው ውህደት የላላ ነበር። በመሆኑም በተረቀቀው ህገመንግሥት ላይ መጠነኛ ማሻሻያ በማድረግ ኖርዌይ የራሷ ህገ-መንግሥት እንዲኖራት የተፈቀደላት ሲሆን፣ የውስጥ ጉዳይን በተመለከተ የራሷ መንግሥት ነበራት። የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ግን የሚመራው ከሲዊድን ሲሆን፣ የሁለቱ ሃገራት ንጉሥም ሲዊድናዊ ነበሩ። Eidsvollsbygningen

አገር ፍቅር ስሜትና ኖርዊጅያናዊ ማንነት

Brudeferd i Hardanger (Hans Gude & Adolph Tidemand, © Nasjonalmuseet for kunst, arkitektur og design)

በ1800ዎቹ አጋማሽ ላይ አውሮፓ ውስጥ በሥነ-ጥበብና ባህል ዙሪያ ብሔራዊ የአገር ፍቅር ስሜት ተብሎ የሚጠራ አዲስ ንቅናቄ ተጀመረ። የአገርን ልዩ መገለጫዎች ማሳወቅ ከተቻለም ማጉላትና ውበት ማላበስ አስፈላጊ ሆነ። በኖርዌይ የሃገሪቱ የተፈጥሮ ውበት ጎልቶ ቀረበ፣ እንዲሁም አርብቶና አርሶ አደሩ ሕብረተሰብ እንደ “ዐይነተኛ ኖርዌያዊ” ተደርጎ ተወሰደ። ብሔራዊው የአገር ፍቅር ስሜት በሥነ-ፅሑፍ፣ በሥዕልና በሙዚቃ መልኩ ተንጸባረቀ። በዚያም ወቅት የኖርዌያውያን የብሔራዊ ማንነት ስሜት እየጨመረ መጣ። አብዛኞቹ በኖርዌያዊነታቸው ከሞክራታቸው ብዛት የተነሳ ሃገራቸው ነፃ እንድትወጣ ጠንካራ ምኞት አሳደረባቸው።

ኖርዌያውያን ለበርካታ ክፍለ ዘመናት ከዴንማርክ ጋር ተዋህደው በመቆየታቸው የኖርዌይ የፅሑፍ ቋንቋ ዴንማርኛ ነበር። በአሁኑ ወቅት ቡክሞል (bokmål) ተብሎ የሚጠራው የፅሑፍ ቋንቋ ዴንማርኛን በመሞርከዝ ተሻሽሎ የቀረበ ነው። ብሔራዊው የአገር ፍቅር ስሜት በተስፋፋበት ዘመን በርካታ ኖርዌያውያን ዴንማርክኛ ቋንቋን ያልተመረኮዘ የራሳችን የፅሑፍ ቋንቋ ሊኖረን ይገባል ባዮች ነበሩ። በመሆኑም ኢቫር ኦስን (Ivar Aasen) የተባለ የቋንቋ ተመራማሪ ኖርዌይ ውስጥ በመዘዋወር በሃገሪቱ ውስጥ ከሚነገሩ የቋንቋ ዜዬዎች የተለያዩ ምሳሌዎችን በመሰብሰብ ኒ ኖሽክ (አዲስ ኖርዌይኛ) የተሰኘ የፅሑፍ ቋንቋ ፈጠረ። ኒኖርሽክና ቡክሞል ከ1800ዎቹ ጀምሮ ይበልጥ እያደጉ የመጡ ቋንቋዎች ቢሆኑም ኖርዌይ አሁንም ከሳሚኛና ከክቬንኛ በተጨማሪ ሁለት ዓይነት ኖርዌይኛ የስራ ቋንቋ አሏት።

ኖርዌይን በኢንዱስትሪ ማሳደግ

Fabrikkarbeidere 1880, (Oslo Museum, fotograf: Per Adolf Thorén)

በመካከለኛው 18ኛው ክፍለ ዘመን ወደ 70 በመቶ የሚጠጋዊ ህዝብ በገጠራማው የኖርዌይ ክፍል ይኖር ነበር። በብዛት በመሬት ማልማትና አሳ ማጥመድ ስራ ላይ የተሰማሩ ነበሩ። ለብዙዎች ኑሮ ከባድ ነበር። የህዝብ ቁጥር ስለጨመረ ለሁሉም በቂ መሬትና ሥራ አልነበረም። በተመሳሳይ ወቅት በከተማዎች ዉስጥ ለውጥ ተፈጠረ። ብዙ ፋብሪካዎች በከተማዎች ስለተመሰረቱ ስራ ለማግኘት ብዙዎች ወደ ከተማ ፈለሱ። ለብዙ ሰራተኛ ቤተሰቦች ኑሮ በከተማ ከባድ ነበር። ረጅም የስራ ሰአትና የኑሮ ሁኔታው መጥፎ ነበር። በብዛት ወላጆች ብዙ ልጆች ሲኖራቸው፣ እና ብዙ ቤተሰቦች ባንድ ትንሽ ቤት ውስጥ መኖር ያልተለመደ አልነበረም። ብዙ ህፃናትም በፋብሪካዎች ውስጥ በመስራት ቤተሰቦቻቸውን መደጎም ነበረባቸው። ብዙዎችም ከሀገር ውጭ ስኬታማ ለመሆን ሞክረው ነበር። ከ1850 እስከ 1920 ከ800 000 በላይ ኖርዊጂያኖች ወደ አሜሪካ ተሰደው ነበር።

ነፃና በራስ የሚተዳደር አገር

የኖርዌይና የስዊዲን አንድነት በ1905 ዓ.ም (እ.ኤ.አ) ፈረሰ። በኖርዌይ የተወካዮች ምክር ቤትና በስዊድን ንጉሥ መካከል ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ፖለቲካዊ አለመግባባት በመኖሩ በሃያኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ በርካታ ኖርዌያውያን ሃገራቸው ራሷን የቻለች ነፃ ሉዓላዊት ሃገር መሆን አለባት ይሉ ነበር። በመሆኑም ጁን 7፣ 1905 (እ.ኤ.አ) የኖርዌይ የተወካዮች ምክር ቤት የስዊዲኑ ንጉሥ ከእንግዲህ የኖርዌይ ንጉሥ አይደሉም በማለት አዋጅ በማውጣቱ በሁለቱ ሃገራት መካከል የነበረው አንድነት ፈረሰ። ውሳኔው ስዊድንን እጅግ በማስቆጣቱ ጦርነት ሊፈነዳ ተቃርቦ ነበር። ይሁንና በዚያው ዓመት በተካሄዱ ሁለት ህዝበ-ውሳኔዎች አማካይነት አዲስቷ ኖርዌይ ነፃ ወጥታ በንጉሣዊ ሥርዓት እንድትተዳደር ተወሰነ። የዴንማርኩ ልዑል ካርል አዲሱ የኖርዌይ ንጉሥ ሆነው ተመረጡ። ልዑሉ የኖርዌይ ንጉሣዊ ቤተሰብ ስም ሃኮንን በመያዝ ንጉስ ሃኮን 7ተኛ ተብለው ከ1905 (እ.ኤ.አ) እስከ ዕለተ ሞታቸው 1957 (እ.ኤ.አ) ድረስ ነገሡ።

1900 ክፍለ ዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ

Vannkraftverk

በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ላይ ኖርዌይ ከውሃ ኃይል አሌክትሪክ ማመንጨት ጀመረች። በመሆኑም በርካታ እንዱስትሪዎች ተቋቋሙ። የሰው ኃይል ፍላጐት እያደገ መጣ፤ ከተሞችም ማደግ ጀመሩ። በዚሁ ወቅት የግል ኩባንያዎች የውሃ ኃይል ማመንጫዎችን እንዲገነቡ ነገር ግን የውሃ ኃይል ሀብት የህዝብ እንዲሆን የሚደነግግ ልዩ ህግ ወጣ።

ከ1914 እስከ 1918 በነበሩት ዓመታት አውሮፓ በአንደኛው የዓለም ጦርነት የታመሰችበት ጊዜ ነበር። ምንም እንኳን ኖርዌይ በጦርነቱ ላይ ቀጥተኛ ተሳታፊ ባትሆንም ጦርነቱ ያደረሰባት የኢኮኖሚ ጫና ግን ጉልህ ነበር። በመሆኑም ኖርዌይ የሸቀጣ ሸቀጦች ለምሳሌ የእህል፣ ቡና እና ስኳር ከፍተኛ እጥረት ስላጋጠማት እነዚህን ሸቀጦች በራሽን ለማከፋፈል ተገዳ ነበር። በ1930ዎቹ አውሮፓና አሜሪካ የኢኮኖሚ ቀውስ ነበር። በርካቶች ሥራቸውንና የመኖሪያ ቤቶቻቸውን አጥተዋል። በዚህ ወቅት ኖርዌይ ውስጥ የነበረው ሁኔታ እንደሌሎች ሃገሮች የከፋ ባይሆንም እነዚያን ጊዜያት “ከባድ የ1930ዎቹ ዓመታት” በማለት እናስታውሳቸዋለን።

የሁለተኛዉ ዓለም ጦርነት ከ1939|1940- 1945

Stortinget med tysk banner 1940-45, (Oslo Museum, ukjent fotograf)

ሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተጀመረው በሴፕቴምበር 1939 ጀርመን ፖላንድን ስትወር ነበር። የጀርመን ሠራዊት በአፕሪል 9፣ 1940 ኖርዌይን ተቆጣጠረ። ውግያው ኖርዌይ ውስጥ ከተካሄደ ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ኖርዌይ ተማረከች። የኖርዌይ ንጉሥና መንግሥታቸው ወደ እንግሊዝ አገር በመሰደድ ኖርዌይ ነፃነቷን እንድታገኝ ከዚያ ሆነው መታገል ቀጠሉ። በዚህ ጊዜ ኖርዌይ ስትገዛ የነበረዉ ከጀርመን ጋር ወዳጅነት ባለውና ዲሞክራሲያዊ ባልሆነ መንገድ በተመረጠ በቪድኩን ኪዊስሊንግ የሚመራ መንግሥት ነበር።

ምንም እንኳ በኖርዌይ ምድር ላይ ብዙ ጦርነቶች ባይደረጉም በርካታ የነፃነት ታጋዮች የህቡዕ የማክሸፍ ስራ መስራት፣ የተለያዩ ህገ-ወጥ ጋዜጦችን በማሳተም፣ የህዝብ እምቢተኝነትና ሠላማዊ ተቃውሞን በማደራጀት የጀርመን ወራሪ ሃይልን ይታገሉ ነበር። በዚህ የተቃውሞ ትግል ውስጥ የተሳተፉ በርካታ ሰዎች ከሃገራቸው ለመሰደድ ተገደዋል። ወደ 50,000 የሚጠጉ ኖርዌያውያን በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ወደ ስዊድን ተሰደዋል። በሰሜን ኖርዌይ በርካታ ሰዎች የተገደሉ ሲሆን፣ ጀርመኖች ለቀው የወጡባቸው አብዛኛው የፊንማርክና ሰሜን ትሮምስ አካባቢዎች በከፍተኛ ደረጃ ፈራርሰው ነበር። የሶቪዬት ጦር ሠራዊት በአካባቢው የነበሩትን ሃብቶች እንዳይጠቀምባቸው ለማድረግ አብዛኛዉቹ ህንፃዎችና መሠረተ ልማቶች በሂትለር ትዕዛዝ እንዲቃጠሉ ተደረገ።

ኖርዌይ በዘመናዊ ጊዜ

En oljeplattform

ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ሃገሪቷ እንደገና መገንባት ነበረባት። ከፍተኛ የእቃ አቅርቦት እጥረትና የመኖሪያ ቤቶች ችግር ህዝቡን አጋጠመዉ ። ሃገሪቱን በተቻለ መጠን በፍጥነት መልሶ ለመገንባት ከሌሎች ሃገሮች ጋር ትብብርና ወዳጅነትን ማጠናከር አስፈላጊ ነበር። በተጨማሪም መንግሥት ኢኮኖሚውንና የዕለት ፍጆታዎችን በጥብቅ ይቆጣጠር ነበር።

ጦርነቱ ልክ እንዳበቃ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ተመሰረተ። የተመድ ዋነኛ ዓላማ ለዓለም ሠላምና ለፍትህ መሥራት ነው። ኖርዌይ ድርጅቱን በኖቬምበር 1945 ከተቀላቀሉ ቀዳሚ ሃገራት መካካል አንዷ ናት። የተመድ የመጀመሪያው ዋና ፀሐፊ ኖርዌያዊ ትርይግቨ ሊየ ነበር።

አሜሪካ በጦርነቱ ለተጐዱ የአውሮፓ ሃገራት የገንዘብ ድጋፍ አቀረበች። ይህ የገንዘብ እርዳታ ማርሻል ፕላን በመባል የሚታወቅ እና ድጋፍ በሚያገኙ ሃገሮች ላይ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ለውጦች የማድረግ ግዴታን የሚያካትት ነበር። ኖርዌይ ወደ ሦስት ቢሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ እርዳታ ከዩናይትድ ስቴትስ አገኘች። በ1949 ኖርዌይ ከሌሎች አሥራ አንድ ሃገሮች ጋር በመሆን የአትላንቲክ ስምምነትን ተፈራረመች። ይህ ስምምነት ለሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን (ኔቶ) መመሥረት መሠረት የጣለ ነው። ኖርዌይ ከምዕራብ አውሮፓ ሃገሮችና ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር የመሰረተችው ጥብቅ ግንኙነት እስከ አሁንም ድረስ ዘልቋል።

በ195ዐዎቹና 196ዐዎቹ የኖርዌይ ኢኮኖሚ በአንፃራዊነት ጠንካራ ነበር። በመሆኑም ዜጐች የተሻለ ህይወት መምራት እንዲችሉ መንግሥት በርካታ ለውጦችን አደረገ። በ196ዐዎቹ በርካታ ኩባንያዎች የነዳጅ ዘይትና የነዳጅ ጋዝ ከኖርዌይ የባህር ዳርቻ ቆፍረው ለማውጣት ፍላጎት ነበራቸው። ከ5ዐ ዓመታት በፊት ከውሃ ኃይል የኤሌክትሪክ ኃይልን ለማመንጨት እንደተደረገው ሁሉ የነዳጅ ዘይት ሃብት የህዝብ እንዲሆን፣ ነገር ግን የግል ኩባንያዎች የነዳጅ ዘይት ፍለጋ፣ ቁፋሮና ምርትን በተመለከተ በጊዜና በቦታ የተገደበ የመግዛት መብት ተሰጣቸው። የነዳጅ ዘይት በሰሜን ባህር ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘው በ1969 ሲሆን፣ ከዚያ ጊዜ ወዲህ ኖርዌይ የነዳጅ አምራችና የነዳጅ ዘይት ወደ ውጭ የምትልክ አገር ለመሆን በቅታለች። ይህ ለሃገሪቱ ኢኮኖሚ ያለው አስተዋፅኦ በጣም ከፍተኛ ነው።

በተጨማሪም ለዛሬይቱ ኖርዌይ ዕድገት በተለያዩ ጊዜያት የተከሰቱ ህዝባዊ ንቅናቄዎች ከፍተኛ አስተዋፅኦ ነበራቸው። በተለይ የተደራጁ የሠራተኞች ንቅናቄዎችና የሴቶች ንቅናቄ ቁልፍ ሚና ነበራቸው። የሠራተኞች ንቅናቄ መሠረቱ ከ16ዐዐዎቹ ቢሆንም በጣም የተጠናከረው ግን በ188ዐዎቹ የኢንዱስትሪ ሥራ ቦታዎች በተስፋፉበት ጊዜ ነበር። ይህ ንቅናቄ በ192ዐዎቹ ይበልጥ እየተጠናከረና ተፅዕኖው እየጐላ ሄደ። የሠራተኞች ማህበራት ንቅናቄ ሠራተኞች የተሻለ የሥራ ሁኔታ እንዲመቻችላቸው የታገለ ሲሆን ከእነዚህም ውስጥ የሥራ ቀናትን ማሳጠር፣ በሥራ ቦታ የተሻለ የደህንነት ሁኔታዎችን ማመቻቸት፣ የጤና ኢንሹራንስ ማግኘት እና የሥራ አጦች የገንዘብ ድጋፍ የማግኘት መብትና የመሳሰሉት ይገኙበታል።

የሴቶች ንቅናቄ ደግሞ ሴቶች በህብረተሰብ ውስጥ ሊያገኙት ስለሚገባቸው መብት፣ የፆታ እኩልነት እንዲሁም ለወንዶችና ለሴቶች እኩል ዕድል እንዲኖር ታግሏል። ለሴቶች ንቅናቄ መስፋፋት ዋነኞቹ ምክንያቶች የፍቺ መብት፣ የወሊድ መከላከያ የመጠቀም መብት፣ ፅንስ የማቋረጥ መብትና በራሳቸው ሰውነት ላይ መወሰን የመቻል መብት ናቸው። በ1978 ፅንስ የማቋረጥ ህግ ወጣ። ህጉ ከሌሎች የሴቶች መብቶች በተጨማሪ ፅንስን ከ13 የእርግዝና ሣምንታት በፊት የማቋረጥን መብት ያካትታል። ዛሬ ኖርዌይ ውስጥ ወንዶችና ሴቶች እኩል የሆነ የትምህርት፣ የሥራ፣ ንብረት የመያዝና የመውረስ፣ መድሃኒትና የጤና እንክብካቤ የማግኘት መብት አላቸው።

 

መረጃ

ኖርዌይ በዛሬው ጊዜ

ኖርዌይ በዛሬው ጊዜ ዘመናዊ ዲሞክራሲና በከፍተኛ መደጋገፍ ላይ የተመሰረት መንግስት አላት። በአብዛኛው ሰው ጥሩ ኢኮኖሚ አለው፣ ህዝቡ በንፅፅር ከፍተኛ የትምህርት ደረጃ አለው። ወንዶችም ሴቶችም በሥራ ይሰማራሉ። ህዝቡ የትምህርት፣ ጤንነትና እንዳስፈላጊነቱ የኢኮኖሚ ድጋፍ በሚሰጡ የተለያዩ ህጎችና ስምምነቶች ይተዳደራል።

ባለፉት አስርት ዓመታት በቴክኖሎጂና ኮምፕዩተር ፈጣን ዕድገት ታይቷል። ይህም ለኖርዊጂያን ማህበረሰብ ውጤት አለው። ብዙ የስራ እድሎችን የፈጥራል፣ የስራ ሁኔታ ይለወጣል እንዲሁም የሰው የግል ህይወት ይለወጣል።

ባለፉት አስርት ዓመታት ኖርዌይ የተለያዩ ብሄር ብሄረሰቦች አገር ሆናለች።