ሁለም ሰው ወደ ስራ

ሁለም ሰው ወደ ስራ

በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች በሥራ ላይ እንዲሰማሩ የማድረግ ዓላማ አለ። ኖርዌይ ውስጥ የሥራ አጥነት መጠን በአንፃራዊነት ዝቅተኛ ነው። ስለሥራ አጥ ቁጥር የበለጠ ለመረዳት የሚከተለውን ድረ-ገፅ ይመልከቱ፡-
Se SSBs nettside om Arbeidsledighet.

የኖርዌይ መንግሥት አዳዲስ ሥራዎች የሚፈጥሩ እና ያሉት ሥራዎች እንዳይጠፉ የሚረዱ እንቅስቃሴዎች ላይ በየዓመቱ ከፍተኛ መዋዕለ-ንዋይ ያፈሳል። መንግሥት ከሚወስዳቸው እርምጃዎች ውስጥ ለምሳሌ ያህል፡-

  • ለተወስነ ጊዜ የገንዘብ ችግር ላጋጠማቸው ኩባንያዎች መንግሥት የፋይናንስ ድጋፍ በማድረግ ኩባንያዎቹ እንዳይዘጉ ወይም የሠራተኛ ቅነሳ እንዳያደርጉ ያግዛል።
  • የደሞዝ ድርድር በማድረግና በወለድ ምጣኔ አማካይነት ባለሥልጣናት በህዝቡ ገቢ ላይ ተፅዕኖ ማሳደር ይችላሉ።
  • መንግሥት የኩባንያዎችን ቀረጥና ግብር መቀነስ ይችላል።
  • መንግሥት ብዙ ወይም ጥቂት ሠራተኞችን በመቅጠር በሥራ ቅጥር ላይ ተፅዕኖ ማሳደር ይችላል። ዛሬ ወደ 750,000 የሚጠጉ ሰዎች የመንግሥት ሥራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ።
  • የሥራ ሰዓቶችን መቀነስ ወይም የጡረታ መውጫ እድሜን ዝቅ ማድረግ ይቻላል።

የኖርዌይ ሠራተኛና ማህበራዊ ዋስትና አገልግሎት (ናቭ)
መንግሥት በናቭ አማካኝነት ለተለያዩ የሰዉ ኃይል ገበያ ኮርሶች የሚውል ብዙ ገንዘብ ያወጣል። እነዚህ ኮርሶች ተሳታፊዎች ሥራ ለማጝነት የሚረዳቸው ብቃት እንዲኖራቸው ይረዳሉ። በተጨማሪም ተሳታፊዎች ኮርሶቹን በሚከታተሉበት ጊዜ የሥራ አጥነት አበል ወይም የገንዘብ ድጋፍ ይሰጣቸዋል።ናቭ የደሞዝ ድጐማዎችን ሊያደርግ ይችላል። ይህም ማለት ሥራ ፈላጊው በጊዜያዊነት ወይም በቋሚነት የሚያስቀጥረው ከሆነ ለሠራተኛው የሚከፈለውን ደሞዝ ከቀጣሪው ጋር በመጋራት ይከፍላል።

ሁሉን አቀፍ የስራ ህይወት ስምምነት (IA-avtalen) በተመለከተ ናቭ ከብዙ አሠሪዎች ጋር ተባብሮ ይሰራል።ከዚህ ስምምነት ጀርባ ያለዉ ሃሳብ፡-

  • መንግሥትና አሠሪዎች የረጅም ግዜ ህመም ፍቃድ ላይ ላሉ ሠራተኞች በቀላሉ ወደ ሥራ መመለስ እንዲችሉ ማድረግ
  • መንግሥትና አሠሪዎች አካል ጉዳተኞች ሥራን በቀላሉ መሥራት የሚችሉበትን መንገድ ማመቻቸት
  • በዕድሜ የገፉ ሠራተኞች ለረጅም ጊዜ መሥራት እንዲችሉ

ኖርዌይ ዉስጥ የቤተሰብ አንድነት የመሰረቱ አዲስ ፍልሰተኞች በሚኖሩበት ወረዳ (ኮሚዩነ) የመሰናድዖ መርሀ ግብር ይሰጣቸዋል። የዚህ መርሀ ግብር ተሳታፊዎች የኖርዌይኛ ቋንቋ እና ህብረተሰብ ትምህርት በነጻ ያገኛሉ። በተጨማሪም የቋንቋ ልምምድ ማድረግ እንዲችሉ በተለያዩ የሥራ ቦታዎች ወይም ድርጅቶች ውስጥ ይመደባሉ። የመሰናድዖ መርሀ ግብሩ ዓላማ ተሳታፊዎቹን ለሥራ ወይም ለትምህርት ብቁ ማድረግ ነው። ይህ መርሀ ግብር የሙሉ ሰዓት ሲሆን ለሁለት ዓመት ይዘልቃል። ተሳታፊዎች የመሰናዶ መርሀ ግብር አበል ይሰጣቸዋል።

ለረጅም ጊዜ ሥራ ሳያገኙ በማህበራዊ የገንዘብ ድጋፍ የሚኖሩ ሰዎች በኖርዌይ ሠራተኛና ማህበራዊ ዋስትና አገልግሎት (ናቭ) በኩል ስራ ማስገኛ መርሀ ግብር ላይ የመሳተፍ ዕድል ይሰጣቸዋል። ይህ መርሀ ግብር ለእያንዳንዱ ተሳታፊ ፍላጐት የሚስማማ ትምህርትና ስልጠና በመስጠት የሥራውን ዘርፍ በቀላሉ እንዲቀላቀሉ ያግዛል። የስራ ማስገኛ መርሀ ግብሩ ብዙ ጊዜ እስከ አንድ ዓመት የሚደርስ የሙሉ ሰዓት መርሀ ግብር ሲሆን ተሳታፊዎች የተሳትፎ አበል ይሰጣቸዋል።

በማንበብ፣ በመፃፍ፣ በሂሳብና በኮምፒውተር አጠቃቀም እንዲሁም በኖርዌይኛ ወይም በሳሚ ቋንቋ ዙሪያ ተጨማሪ ትምህርትና ሥልጠና ለሚያስፈልጋቸው ሠራተኞች ሥልጠና የሚያዘጋጁ ኩባንያዎች ወይም ድርጅቶች የገንዘብ ድጋፍ ማግኘት ይችላሉ። እንደዚህ ዓይነት ሥልጠናዎች ሠራተኛው በሥራዉ ላይ ብቁ እንዲሆን ወይም ሌላ ሥራዎችን መፈለግ እንዲችል ያደርጋሉ።